በአዲስ አበባ የቤንዚን 91.14 ብር በሊትር፤ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 100.20 ብር በሊትር ሆኗል
የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ዛሬ ምሽት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫው ከዛሬ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በሁሉም የነዳጅ አይነቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት በቤንዚን፣ በኬሮሲን፣ በነጭ ናፍጣ፣ በቀላል ጥቁር ናፍጣ እና በከባድ ጥቁር ናፍጣ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል።
የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ጭማሪ ተደረገው ተግባራዊ ተደረገውን የማክረሮ ኢኮኖሚ ማስተካከያ ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ እንደሆነም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በእነዚህ መሠረታዊ ምክንያት ሀገራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ እግባብ መጠነኛ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓል ያለው ሚኒስቴሩ የሊኮኖሚውን ወቅታዊ ሁኔታና የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ የዋጋ ማስተካከያ ስትራተጂ ተነድፎ ሥራ ላይ እንዲውል በመንግሥት ተውስኗል ብሏል።
በስትራቴጂው መሠረት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከታየው ጭማሪ ተጠቃሚው ህብረተሰብ እጅግ አነስተኛ የሆነ ዋጋ በየሶስት ወሩ እየከፈለ፤ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን ከፍያእ እየደጎመ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የተሟላ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግ መሆኑን አስታውቋል።
በዚሁ መሠረት የአለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያ በየሶስት ወሩ የሚደረግ ሲሆን መንግሥት በነዳጅ ዓይነት የሚለያይ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ጥቅል ድጎማ ያደርጋል ብሏል።
ለአብነትም የአለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ በተሰራው ስሌት የተገኘው የቤንዚን የችርቻሮ ዋጋ አዲስ አበባ ላይ ብር 117.28 በሊትር ሲሆን በሥራ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በብር 34,88 ወይም የ42 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በመጀመሪያ ዙር በቤንዚን የችርቻሮ ዋጋ ላይ ከታየው ጭማሪ ብር 34.68 ውስጥ ተጠቃሚው ብር 8.54 በሊትር ወይም 24.60 በመቶ ብቻ እንዲከፍልና የሚደረግ ሲሆን ቀሪው ብር 26.14 በሊትር ወይም 75.4 በመቶ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት በመንግሥት እየተደጎመ እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በሀዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ የቤንዚን ዋጋ ብር 91.14 በሊትር እንደሚሆን ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያመላከተው።
በተመሳሳይ ሁኔታ በስሌት የተደረሰበት የነጭ ናፍጣ የችርቻሮ ዋጋ አዲስ አበባ ላይ ብር 117.00 በሊትር ሲሆን በሥራ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የብር 33.26 በሊትር ወይም የ39.7 መቶኛ ጭማሪ አሣይቷል።
በነጭ ናፍጣ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ከታየው ከዚህ ጭማሪ ውስጥ ተጠቃሚው ብር 6.54 በሊትር ወይም 19.7 በመቶ ብቻ የሚከፍል ሲሆን ቀሪው ብር 26.72 በሊትር ወይም 80.3 በመቶ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት በመንግሥት እየተደጎመ የሚቀጥል ይሆናል።
ይህንን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ የነጭ ናፍጣ አዲሱ ዋጋ ብር 90.28 በሊትር እንደሚሆንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ ላይ የሚውለው የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ፤
ቤንዚን …………………………… ብር 91.14 በሊትር
ነጭ ናፍጣ……………………… ብር 90.28 በሊትር
ኬሮሲን ……………………………. ብር 90.28 በሊትር
የአውሮፕላን ነዳጅ ………………… ብር 77.76 በሊትር
ቀላል ጥቁር ናፍጣ………………… ብር 100.20በሊትር
ከባድ ጥቁር ናፍጣ…………………. ብር 97.67 በሊትር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የዋጋ ማስተካከያውን ተከትሎ መንግሥት በሶስት ወራት ብቻ በአማካይ ብር 33.00 ቢሊየን የድጎማ ወጪ የሚከፍል መሆኑነም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የአለም ዋጋ አሁን ባለበት መጠን የሚቀጥል ከሆነ መንግስት በአንድ ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ለነደጅ ድጎማ ወጪ የሚያወጣ ይሆናል ብሏል።