በኢትዮጵያ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተጋላጭ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ እስከ 40 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟት እንደነበር ያውቃሉ?
በካራቆሬ ፣ላንጋኖ እና ሰርዶ ላይ ያጋጠሙት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ከባድ ጉዳት ያደረሱ አደጋዎች ሆነው አልፈዋል
በኢትዮጵያ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተጋላጭ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
በሚያደርሰው አደጋ ምክንያት አስፈሪ የሆነው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከሰሞኑ በኢትዮጵያዊን ዘንድ ትኩረት ስቧል፡፡
በተለይም ባሳለፍነው ሳምንት በአፋር እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ 4 ነጥብ 9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ ርዕደ መሬት ካጋጠመ በኋላ ንዝረቱ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ተሰምቷል፡፡
አል-ዐይን አማርኛ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በርዕደ መሬት ምህንድስና ሙያ ዘርፍ ጥናቶችን በማድረግ ከሚታወቁት ዶክተር መሰለ ሀይሌ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ዶክተር መሰለ የሶስተኛ ድግሪያቸውን ከጃፓኑ ቶኪዮ ዩንቨርሲቲ በመሬት መንቀጥቀጥ ምህንድስና ያገኙ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲም የጂኦ ቴክኒክስ እና መሬት መንቀጥቀጥ ምህንድስና ትምህርት ዘርፍ ለዓመታት ከማስተማራቸው ባለፈ በርካታ ጥናቶችን በማድረግም ይታወቃሉ፡፡
ዶክተር መሰለ በኢትዮጵያ ምህንድስና ባለሙያዎች ማህበር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉ መሀንዲሶች መካከልም ዋነኛው ናቸው፡፡
ሙሉ ቃለ መጠይቁን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል፡፡
አል-ዐይን፡- የመሬት መንቀጥቀጥ ምን ማለት ነው? እንዴትስ ይከሰታል?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- መሬት መንቀጥቀጥ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ በከርሰ ምድር ውስጥ የተከማቸው ኃይል በድንገት ሲለቀቅ የሚፈጠር ክስተት ነው። ክስተቱ የመሬት ውስጣዊ አካላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡
አል-ዐይን፡- የመሬት መንቀጥቀጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ይመስላል?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- ትልቅ እና አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያጋጥማቸው በፓስፊክ ውቂያኖስ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡
መካከለኛ አደጋ የሚያጋጥማቸው ደግሞ ሂማሊያ ተራራ አካባቢ ያሉ ሀገራት እንደ ቱርክ፣ ሶሪያ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ ናቸው፡፡ በመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ውስጥ የሬክተር ስኬሉ 7 እና ከዛ በላይ ከሆነ ጉዳት ያደርሳል፡፡ እስካሁን በዓለም የመሬት መንቀጥቀጥ ታሪክ ከ10 ሬክተር ስኬል በላይ አጋጥሞ አያውቅም፡፡
አል-ዐይን፡- በኢትዮጵያ ለመሬት መንቀጥቀጥ የበለጠ ተጋላጭ የሆነው አካባቢ የትኛው ነው?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- በኢትዮጵያ ሁኔታ የስምጥ ሸለቆ በሚባሉ አካባቢዎች ያሉ ቦታዎች ለመሬት መንቀጥቀጥ የበለጠ ተጋለጭ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚባለው ከቀይ ባህር ተነስቶ መቀሌ፣ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ አንኮበር፣ ደብረብርሃን፣ አዋሽ፣ አዳማ፣ መተሃራ ፣ፈንታሌ፣ መቂ፣ ዝዋይ፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፣ አዲስ አበባ (አቃቂ ቃሊቲ እና አካባቢው) ናቸው፡፡
አል-ዐይን፡- የስምጥ ሸለቆ የተባሉት አካባቢዎች ሁሉ ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ናቸው ማለት እንችላለን?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- በስምጥ ሸለቆ በተባሉ አካባቢዎች ስር ያሉ ቦታዎች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ዋናው አደጋው የተፈጠረበት ቦታ ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ በፈንታሌ ተራራ ላይ 4 ነጥብ 9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሟል፡፡ የዚህ አደጋ ንዝረት እስከ አዲስ አበባ እና ደሴ ኮምቦልቻ ድረስ ተሰምቷል፡፡ ነገር ግን በአደጋው ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ቤቶች ፈርሰዋል፣ መሬት ተሰንጥቋል፡፡ ስለዚህ ጉዳቱ የሚጨምረው አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ባሉ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ እየራቀ በሄደ ቁጥር አደጋውም እየቀነሰ ነው የሚመጣው፡፡
አል-ዐይን፡- የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኢትዮጵያ ምን አይነት ታሪክ አለው?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- የተመዘገቡ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ 1898 ዓ.ም ላይ ነበር የተከሰተው፡፡ አደጋው ያጋጠመው ላንጋኖ ላይ ነበር፡፡ አደጋው 6 ነጥብ 8 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ ሲሆን በወቅቱ በአዲስ አበባ የነበሩ ቤተ ክርስቲያናትን አፈራርሶ ነበር፡፡
ሁለተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ያጋጠመው በ1953 ዓ.ም ሲሆን ከአዲስ አበባ-ደሴ ባለው ዋና መስመር ላይ ልዩ ስሙ ካራቆሬ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ አጋጥሞ ነበር፡፡ ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ 6.75 ሬክተር ስኬል ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ ቦታዎችን በተለይም ማጀቴ፣ ኮምቦልቻ- ደሴ እና የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የነበሩ መኖሪያ ቤቶችን እንዲፈርሱ ምክንያት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ሶስተኛው አደጋ ደግሞ በ1960 ዓ.ም ሰርዶ ተብሎ በሚጠራው የአፋር ማህበረሰብ በሚኖርበት ቦታ ሰመራ አካባቢ 6.4 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ አደጋ አጋጥሞ ቤቶችን አውድሞ አልፏል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ እስከ 6 ነጥብ 8 ሬክተር ስኬል የተመዘገቡ ከ30-40 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ያጋጠማት ሲሆን ብዙዎቹ የከፋ አደጋ ያላደረሱት ህንጻዎችን ስላልሰራን ነው፡፡
አል-ዐይን፡- አሁን ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኢትዮጵያ አስጊ ነው ማለት እንችላለን?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- አዲስ አበባ ከዋና የስምጥ ሸለቆ ከተሞች ራቅ ያለች ብትሆንም ረጃጅም ህንጻዎች ስላሉ ከሌሎች ከተሞች የበለጠ የጉዳት ተጋላጭ ናት፡፡
የ1960ው ሰርዶ ላይ ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በስፍራው ይኖሩ ነበር ከተባሉ 400 ነዋሪዎች ውስጥ 39 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከ100 በላይ ሰዎችም ቆስለው ነበር፡፡ ሰርዶ ላይ ከነበሩት ቤቶች ውስጥ አንድም ቤት አልተረፈም ነበር፡፡ ይህ አደጋ ያልከፋው በወቅቱ ብዙ ቤቶች እና ፎቆች ስላልነበሩ ነው፡፡
አል-ዐይን፡- የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሲያጋጥም ዜጎች ምን አይነት ጥንቃቄ ነው መውሰድ ያለባቸው?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- አደጋ ሲያጋጥም ቤት ወዲያው አይፈርስም፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ እስከ 10 ሰከንድ ነው ሊቆይ የሚችለው፡፡ ስለዚህ የሚሻለው ካለንበት ቦታ ለመሮጥ አለመሞከር ነው፡፡ ከወንበሮች ስር መሆን፣ ለምሳሌ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከሆንን ጠንከር ያሉ ነገሮችን መጠለል ለምሳሌ አልጋ ስር፣ ጠረንጴዛ ስር፣ በር ስር መንቀጥቀጡ እስከሚያልቅ ባለንበት መቆየት አለብን፡፡ ይህን አደጋ ሮጠን ልናመልጥ አንችልም፡፡ ትክክለኛው ነገር ለመረጋጋት መሞከር እና ህንጻ ባንድ ጊዜ ስለማይፈረስ በየት በኩል እየፈረሰ እንደሆነ ማየት የተሻለ ደህንነት መፈለግ ነው ያለብን፡፡ ብዙ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ በዙር ሊከናወን ይችላል የመጀመሪያው ዙር ካለቀ በኋላ በመውጣት ወደ ባዶ ቦታ ከህንጻ እና ከሚወድቁ ነገሮች መራቅ፣ እሳት አደጋዎች እንዳይነሱ የምግብ ማብሰያ እና ሌሎች የተያያዙ እሳቶች ካሉ ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡
አል-ዐይን፡- አደጋው ቢያጋጥም ሊደርሱ የሚችሉ ተጨማሪ ጉዳቶችን እንዴት መቀነስ ይቻላል?
ዶክተር መሰለ ሀይሌ፡- በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ከተጎዱ ሀገራት መካከል ፓኪስታን፣ አሜሪካ፣ ጃፓን እና ሌሎችንም ሀገራት አደጋዎቹ ያደረሱትን ጉዳቶች ጎብኝቻለሁ፡፡ ብዙ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ሀገራት አደጋው ሊያደርሰው የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ችለዋል፡፡ ጃፓኖች በዓመት አንድ ቀን የተቆረጠ ቀን አላቸው፣ ይህ ቀን አደጋ ቢያጋጥም መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ የሚለማመዱበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በየሚዲያዎቻቸው እና ትምህርት ቤቶች ላይ ስለ አደጋ መከላከል፣ ራስን ከድንገተኛ አደጋዎች ስለመጠበቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡
እኛ ሀገር አዳጋ ቢያጋጥም ጉዳቱ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ የህንጻዎቻችን ጥራት ያሳስባል፣ ዜጎች ስለ መሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ያላቸው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የተቋማት ዝግጁነቶች አነስተኛ ናቸው፡፡ የተገነቡ ህንጻዎችን ጥራት ዳግም መፈተሸ፣ እንደ ሆስፒታል፣ የዕምነት ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ብዙ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው ህንጻዎችን ጥራት በሚገባ መፈተሸ እና ችግር ካለም ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሁሌም ቢሆን አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ የሚዘጋጁ ተቋማት መኖር አለባቸው፣ የሀገር መሪዎች የሚኖሩባቸው ህንጻዎች፣ እንደ ሆስፒታል፣ ወታደራዊ እና የደህንነት ተቋማት ህንጻዎች ጥራታቸው አስተማማኝ መሆን አለበት፣ ጉዳቶችን ለመቀነስ መንግስት፣ መሀንዲሶች እና የህንጻ ባለቤቶች በህንጻዎች ላይ ቁጥጥር እና ተከታታይ ማስተካከያዎችን ማድረግ አለባቸው፡፡