ትግራይን በፌደራል የሚወክሉ የፓርላማ ተመራጮች ሀገርአቀፍ ምርጫ ሲደረግ ይመረጣሉ-ኮሚሽኑ
“እኔ የኢህአፓ እንጅ የሕወሓት አባል አልነበርኩም” የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም
ኮሚሽኑ ህገ መንግስቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ “የአንድን ሉዓላዊ ክልል የመምረጥ መብት የማገድ ሥልጣን አለው” አይልም
ኮሚሽኑ፡ ህገ መንግስቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ “የአንድን ሉዓላዊ ክልል የመምረጥ መብት የማገድ ሥልጣን አለው” አይልም
በኢትዮጵያ በነሐሴ 2012 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ የነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት የቅድመ ምርጫ ተግባራትን ማከናወን አልቻልኩም በማለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደማይካሄድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ከዚህም በኋላ የሕገ መንግስት ትርጉም ተሰጥቶበት ምርጫው እንዲራዘም ተወስኗል፡፡
የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አድርጎት በነበረው ስብሰባ ብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም የ2012 ሀገር አቀፍ ምርጫን ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት አላሳየም ሲል መወንጀሉ ይታወሳል፡፡ የክልሉ ምክር ቤትም ምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም የክልል ምክርቤት ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡ የትግራይ ክልል አሁን ምርጫ ካደረገ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ይሳተፋል፡፡ የኮሚሽኑን ዕጣ ፋንታና ሕጋዊነት በተመለከተና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ አል ዐይን ከትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አል ዐይን ፡- በትግራይ ክልል አሁን ምርጫ የሚደረግ ከሆነ ከ9 እስከ 10 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ በሀገር ደረጃ ምርጫ እንደሚደረግ መንግስት ገልጿል፡፡ታዲያ በሀገር አቀፉ ምርጫ ላይ የትግራይ ክልል ይሳተፋል ወይስ አይሳተፍም?
ሙሉወርቅ ፡- ውሳኔው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ነው፡፡እና ከዛ ቀደም ብሎ ምርጫ በማካሄድና ባለማካሄድ በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለመስማማቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁሉም ሰው የሚውቀው ነው፡ስለዚህ በሕገ መንግስት ዙሪያ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር፤ ጥያቄዎቹ የተፈቱበት አግባብ በትግራይ መንግስትም ሆነ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የክልሉ ምክር ቤት ይህንን የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም ተገዷል፡፡ምክንያቱም በሕገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫዎችን የመከታተል ሥልጣን አለው፡፡የተሰጠውን ሥልጣንም ሊወጣ አልቻለም ጥያቄው ቀርቦለታል፡፡ በተገቢው መጠን ማካሄዴ አልተቻለም፡፡ ጥያቄው ቀርቦለታል፡፡ማካሄድ አትችሉም የሚል ውሳኔ ነው የሰጠው፡፡ምርጫ የማካሄድና ያለማካሄድ ፈቃጅ ሰጭ ሃይል የለም፡፡ ምርጫ የሚያካሂድ ድርጅት እንጅ ፈቃድ የሚሰጥና የሚከለክል ድርጅት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ምክር ቤቱ የሰጠውን ሥልጣን ነው የሚያስፈጽመው እንጅ ምርጫ ወሳኝና አድራጊ ፈጣሪ አይደለም፡፡በመንግስት ውሳኔ መሰረት የሚሰራ አካል ነው፡፡ ስለዚህ የትግራይን ሕዝብ የመምረጥ መብት የመከልከል መብት የለውም በሚል ነው ይህንን የምርጫ ኮሚሽን ምክር ቤቱ ሊያቋቁም የተገደደው፡፡በዛ መሰረት የፌዴራሉ መንግስት ምርጫውን እንዳልወደደው ይታወቃል፡፡ ያለመውደድ ሌላ ነገር ሆኖ በሁለቱ መካከል ውይይትና ሥምምነት ቢደረግ ጥሩ ነበረ ሊደረስ ግን አልቻለም፡፡ምርጫው መካሄድ አለበት የለበትም የትግራይ ክልልና የፌዴራል ብቻ አይደለም ጥያቄው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች የሚነሳ ነው፡፡መፍትሔው ምንድነው መሆን ያለበት የሚልም ከግራና ከቀኝ የሚቀርብ ሃሳቦች አሉ፡፡
አል ዐይን ፡- የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ንዑስ አንቀጽ 1 በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል። በዚህ መሰረት ምርጫ ማድረግ የሚችል አንድ ብሔራዊ ተቋም ነው አለ የሚለው የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ሕገ መንግስቱ ከሚለው ጋር አይጋጭም
ሙሉወርቅ ፡- ሕገ መንግስቱ የአንድን ሉዓላዊ ክልል የመምረጥ መብት የማገድ ሥልጣን አለውም አይልም፡፡ ስለዚህ ያንን አግዳለሁ የሚል ከሆነ ክልሉ ያለው ምርጫ ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫ የሚያካሂድለት የራሱ ድርጅት ማንም አይደለም አፌክት የሚያደርገው ይሄ ክልሉን ነው አፌክት[የሚመለከተው] የሚያደርገው፡፡ የክልሉ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እየተጠበቀለት ነው፤ ሕገ መንግስቱ የጠበቀለት ነው፤ይህንን ማንም መከልከል አይችልም፡፡
አል ዐይን ፡- ራስን በራስ ማስዳደር እንዳለ ሆኖ የክልል ምርጫ ኮሚሽን ማቋቋም ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ጋር አይጋጭም?
ሙሉወርቅ ፡- ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው የሚል ካለ ስለዚህ እርሱ ቢፈርስስ አላደርግም ቢልስ ሀገሪቱ ትታሰራለች ማለት አይደለም፡፡ የሀገሪቱ ሕዝቦች ይታሰራሉ ማለት አይደለም፤ ማንም አፌክት የሚያደርግ አይደለም፡፡የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አካል እንጅ ፈቃጅና ከልካይ አይደለም፡፡ ምርጫ ለማድረግና ላለማድረግ ምርጫው እንዴት ተካሄደና እየተካሄደ ነው የሚል ብቻ ሆኖ ለመታዘብና ለማስፈጸም የቆመ አካል ነው፡፡ እሱ አላስፈጽምም ሲል እንግዲህ የሕዝብ የመምረጥ መብት ይቀራል ማለት አይደለም፡፡
አል ዐይን ፡- ኮሚሽኑ ለዚህ ምርጫ ተብሎ ብቻ የተቋቋመ ነው ወይስ በቀጣይም ይቀጥላል?
ሙሉወርቅ፡- አሁን ገለልተኛና ነጻ የሆነ ታዛቢ መኖር አለበት፡፡ አንድ ምርጫ ታአማኒ እንዲሆን የሚል ለታዛቢዎች ሲባልም አይደለም ነገር ግን በትግራይ ከጣቢያዎች ጀምሮ በህዝብ የተመረጡ ታዛቢዎች አሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመወዳደር ገብተዋል፡፡ እነዚህም የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው እና የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ወደ ክልሉ ታዛቢዎች መምጣት ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለው ጥያቄ ካለፉ ሁኔታዎች እንኳን ታዛቢዎች ኢንቨስተሮችም የተከለከሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይሄ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው የግንኙነት ችግር ፖለቲካ የፈጠረው ነው፡፡ አሁን ግን የትግራይ ህዝብ አምስት ዓመት ስለሞላው በድል ያገኘውን መብት አሳልፎ መስጠት አይፈልግም፡፡ስለዚህ ይህንን አሳልፎ ላለመስጠት፣ ይህንን እንዲሆን ያደረገ ሕዝብ ተከልክለሃል ሊባልም አይገባውም፡፡ ይሄ ብዙ መስዋዕትነት የከፈልኩበት መብቴ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ የደገፈው ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ ለማን ፍላጎት ሲባል ነው የማይካሄደው፡፡ ሕዝቡ አምስት ዓመት የሠጠው ኮንትራት አለ፡፡ ሕጋዊ መንግሰት አቋቁማለሁ የሚል ከሆነ ለዚህ ዋነኛው ነገር መንግስት የሚቋቋመው ለማንም አይደለም ለትግራይ ብቻ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ አልፈልግም አዲስ መንግስት ካለ የትግራይ ህዝብ ምርጫ ነው፡፡ ተገዶ አይደለም የሚያካሂደው ከጫፍ እስከ ጫፍ ሕዝቡ ራሱን በራሱ አደራጅቶ የሚያካሂደው ነው፡፡ ምርጫ ኮሚሽኑ ይህንን ምርጫ ለማከናወን ከ29ሺ በላይ አስፈጻሚዎች፣ታዛቢዎች፣ቅሬታ ሰሚዎች በየደረጃው ያሉበት ነው፡፡ ይሕንን ፖለቲካሊ ማየት ትንሽ ያስቸግራል፡፡
አል ዐይን ፡- ታዛቢዎቹ እነማን ናቸው?
ሙሉወርቅ ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይከተላቸው የነበሩትን ሕጎች በምንም አይነት ሳይዛነፉ ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ስለዚህ ከየቀበሌው ጀምሮ የሕዝብ ታዛቢዎች ተመርጠዋል፡፡ ቅሬታ ሰሚዎች ተመርጠዋል ከጣቢያዎች ጀምሮ፡፡
አል ዐይን ፡- አሁን በትግራይ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ በቀጣይ ዓመት ደግሞ በሀገር ደረጃ ምርጫ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ስለዚህ ሀገር አቀፍ ምርጫው ሲደረግ በፌዴራል ደረጃ ትግራይን የሚወክሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫስ እንደት ይሆናል? ከዚህ በኋላስ እንዴት ነው በሀገሪቱ ተመሳሳይ የምርጫ ሰሌዳ የሚኖረው አሁን በትግራይ ምርጫ ከተደረገ?
ሙሉወርቅ ፡- ይሄ የሚመለከተው ትግራይን ብቻ ነው፡፡ በትግራይና በፌዴራል መንግስታት መካከል የፖለቲካ ድርድር ፣ስምምነትና ሰላም ሲመለስ ሥርዓቱ እንደዚህ ሆኖ ይቀጥላል ተብሎ ዲፋይን ሲያደርግ የሚሆኑ ሁኔታዎች ናቸው ማለት ነው በዚህ ነው ሊመለስ የሚችለው፡፡
አል ዐይን፡- ስለዚህ ምርጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲደረግ ለፓርላማ ተመራጮች ሲባል ድጋሚ ይደረጋል ?
ሙሉወርቅ ፡- ድጋሚ ማድረግ አይጠበቅም፡፡ ይህ ምርጫ የሚመለከተው ትግራይን ብቻ ነው፡፡ በፌዴራል የትግራይ ውክልና ሲፈለግ ሌላ ጉዳይ ይሆናል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የሚወከሉ ሰዎች ምርጫ ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ትግራይን በፌዴራል የሚወክሉ ሰዎችን ለመምረጥ ምርጫ ይካሄዳል ማለት ነው፡፡ ፌዴራል ለሆነው ጉዳይ ፌዴራሉ ይቋቋማል፣የፌዴራል መንግስት ሊቋቋም የሚችለው ከፓርላመንታዊ ዴሞክራሲ ስለሆነ ከፓርላማ የሚወጣ መንግስት ይኖረናል፡፡ ወደ ፓርላማ የሚሄዱ ሰዎች ይመረጣሉ ማለት ነው፡፡ በሹመት ስለማይሆን ትግራይ ያለ ፓርቲዎችም ተፎካክረው ምርጫ ተደርጎ ነው ወደ ፓርላማ የሚላኩት፡፡
አል ዐይን ፡- በሕገ መንግስቱ መሰረት የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ሕጋዊ አይደለም የሚሉ አሉ፣ ምክንያቱም በብሔራዊ ደረጃ አንድ የምርጫ ቦርድ እንደሚኖር ስለሚደነግግ፤ስለዚህ እርስዎ የሚመሩት ኮሚሽን ሕጋዊ የሚሆነው በምን የሕግ አግባብ ነው?
ሙሉወርቅ ፡- ሕጋዊ ነን፡፡ እንግዲህ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ያቋቋመው ነው ሕጋዊ ነው፡፡ የትግራይን የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከተቀበልክ ድረስ የትግራይ[ክልል] የወሰነውን መቀበል አለብህ፤ ትግራይን በሚመለከት ማለት ነው፡፡ ትግራይ አብሮ ወሰነው እንደ ሀገር ያካሂድልኛል ብሎ የመረጠው ወይም አሜን ብሎ የተቀበለው የምርጫ ቦርድ አላስተናግድህም ሲለው ምርጫው ምንድነው መሆን ያለበት?
አል ዐይን ፡- ሕጋዊ የሚዲርጉትን የሕግ አንቀጾች ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
ሙሉወርቅ ፡- እንግዲህ ሕጋዊ ብለን እየሰራን ነው፡፡ ስለወደፊቱ በፖለቲካ ሃይሎች መካከል በሚኖር ድርድር ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ዝም ብሎ ይሄ ነገር በሃይል ይፈታል ምናምን የሚል ነገር አይደለም ያለው፡፡እኔ ሰላም እንዲኖር የምፈልግ ስለሆንኩኘ ማለት ነው፡፡
አል ዐይን ፡- ታዲያ ኮሚሽኑን ሕገ መንግስቱ ይደግፈዋል ማለት ነው?
ሙሉወርቅ ፡- አታካሂዱም ሲል እሽ እሱ ብሎናል፤ እኛ ታዲያ ምን እናድርግ?
አል ዐይን ፡- ምርጫ የሚደረግ ከሆነ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ተሟልተዋል ወይስ ገና ናቸው?
ሙሉወርቅ ፡- የሎጀስቲክ ዝግጅታችን ጥሩ ላይ ነው ያለው፡፡ በወቅቱ እንደርሳለን፡፡ ብዙ ነገሮች ማከናወን ችለናል፡፡ በመርሃ ግብራችን መሰረት እየሄድን ነው፡፡
አል ዐይን ፡- ምርጫውን መቼ ለማድረግ ነው ያቀዳችሁት?
ሙሉወርቅ ፡- ሰሞኑን ዝርዝር መርሃ ግብሩን እናወጣለን፡፡ እና ምርጫ 2012 ነው እንደገባኝ ስለዚህ 2012 መደረግ አለበት፡፡ መስከረም አካባቢ ሊካሄድ ይችላል መስከረም መጀመሪያ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ከፓርቲዎችም ጋር ውይይት ተደርጎ ይወሰናል፡፡
አል ዐይን ፡- መሰረታቸውን ትግራይ ክልል ላይ ያደረጉ ነገር ግን በምርጫው የማይሳተፉ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡
ሙሉወርቅ ፡- ስለማይመለከታቸው ነው እንጅ ከመሃል መሳተፍ የሚፈልጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ልዩነቱ የፈጠረው ይመስለኛል፡፡ ምርጫው መካሄድ የለበትም ያሉት አይሳተፉም፡፡ መካሄድ አለበት የሚሉት ይሳተፋሉ፡፡
አል ዐይን ፡- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምንም እንኳን ከዚህ በፊት ቅሬታዎች ሲነሱበት የነበረ ቢሆንም ምርጫዎችን በማድረግ ልምድ አለውና በዚህ ልታካሂዱ ባሰባችሁት ምርጫ ቦርዱን ታነጋግሩታላችሁ፤ ግንኙነታችሁ ምን ይመስላል?
ሙሉወርቅ ፡- ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም፡፡ የእኛ ኮሚሽን ለክልል ምክር ቤት ነው ተጠሪነቱ፡፡ ክልሉን በሚመለከት የክልል ምክር ቤት አለቃ የለውም፡፡ ልምድን በሚመለከት ልምድ ያላቸው ሰዎቹ ናቸው ተቋሙ ነው የሚለውን ማየት ነው፡፡ ምርጫ ያደረጉትም እኮ እዚህ ትግራይ ውስጥም አሉ፡፡
አል ዐይን ፡- የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወልቃይትና ራያ እልባት ሳይሰጣቸው ወይም የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን ውሳኔ ሳይሰጥ በአካባቢዎቹ ምርጫ መደረግ የለበትም የሚሉ ፓርቲዎችና ቡድኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ምላሽ አለዎት?
ሙሉወርቅ ፡- የትግራይ ክልል ምርጫ መደረግ አለበት ብሏል፡፡ የት ለሚለው ትግራይ ውስጥ ፡፡ስለዚህ ትግራይ ውስጥ ምርጫ ይደረጋል፡፡ የክልሉ መንግስት ምርጫውን ያካሂዳል በክልሉ ውስጥ ክልሉ ውስጥ ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ካለ ይሄ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡
አል ዐይን ፡- ሕገ መንግስት ተጣሰ በሚል የፌዴራል መንግስትም የትግራይ ክልል መንግስትም እርስ በእርስ የቃላት ምልልሶች ውስጥ ገብተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል የሚል ድንጋጌ አለ፡፡ በዚህ መሰረት የዚህ ተቋም ኃላፊ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ናቸው፡፡ እርሶዎ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በተቋቋመ ሌላ ኮሚሽን ( ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ንዑስ አንቀጽ 1 ውጭ) ኃላፊ ነዎት፡፡ በዚህም መሰረት ታዲያ ማነው ሕጋዊ ኃላፊ ማነው ሕገ ወጥ ኃላፊ?
ሙሉወርቅ፡- ትግራይ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ሥልጣኑ የራሱ ነው፡፡ እኔ ከሰዎች ጋር ምንም ጥላቻም የተለየ አመለካከት የለኝም ፡፡የተሰጠኝ ስራ ይህንን እንድፈጽም ነው፡፡ ይህንን ሥራ የማስፈጽምበት መዋቅር ተፈጥሮልኛል፡፡ ስለዚህ ሕጋዊ ተቋም ነው፤ የምመራው መንግስት ያቋቋመው ነው፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ያቋቋመው ተቋማ ሕጋዊ አይደለም ሊባል አይችልም፡፡ስለወ/ሪት ብርቱካን ምን እንደሚያደርጉ ቢናገሩ ይሻላል፡፡ሥልጣኔን ቀምቶኛል የሚሉ ከሆነ እኔ አይደለሁም ማለት ነው፡፡
አል ዐይን ፡- ትግራይ ውስጥ እኮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ አለ፡፡ ነገር ግን ክልሉም ሌላ አቋቋመ፡፡ ይህ እንዴት ይቻላል ሕግን አይጻረርም?
ሙሉወርቅ ፡- እኔ እንጃ በፊት ነበረ፤ እሱ አልሰራ ካለ ሌላ ይፈጠራል፡፡