ቦርዱ የወረርሽኙ ሁኔታ ሳይረጋገጥ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ እንደማያካሂድ አስታወቀ
የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫን በተመለከተ ያቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ
ምክር ቤቱ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ የመስጠት እና ቦርዱ ውሳኔውን ሊያስፈጽም ይገባል የማለት ህጋዊ መሠረት እንደሌለውም ገልጿል
ቦርዱ የወረርሽኙ ሁኔታ ሳይረጋገጥ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ እንደማያካሂድ አስታወቀ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ እንዲያውቅለትም ሆነ ምርጫ እንዲያስፈፅምለት ያቀረበውን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀረ፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት 6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ ለማካሄድ አለመቻሉን ተከትሎ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጠየቀው የህገ መንግስት ትርጉም መሰረት ምርጫው በፌዴሬሽን ምክር ቤት መራዘሙን የገለጸው ቦርዱ የወረርሽኙ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ እንደማያካሂድ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም “ምክር ቤቱ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ህጋዊ መሠረት” እንደሌለው ነው የገለጸው፡፡
“የሰጠውን ውሳኔ እንዳውቅለትም ሆነ ምርጫ እንዳስፈፅምለት ያቀረበውን ጥያቄ አልተቀበልኩም” ያለም ሲሆን የተጠየቀውን የሰው ሀይል፣ የሎጂስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የህግ አግባብ አለመኖሩን አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ “ኮቪድ 19ኝን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈፅም፣ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ነበር ለቦርዱ ጥያቄውን ያቀረበው፡፡
ወረርሽኙ የህዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከ9 ወር እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡
ምክር ቤቱ ያስገባውን የውሳኔ ሃሳብ አስመልክቶ አል ዐይን አማርኛ ከሰሞኑ የቦርዱን የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስን በስልክ አናግሮ ነበር፡፡
“እኛን የሚመለከተው በደብዳቤ ለተገለጸው ጥያቄ ብቻ መልስ መስጠት ነው” ያሉት ወ/ሪት ሶሊያና ክልሉ ምርጫ የሚያስፈጽም አካል እንደሚያቋቁም አስታውቋል መባሉ “መንግስትን እንጂ ቦርዱን” እንደማይመለከት ገልጸዋል፡፡
“አንድ የክልል መንግስት የሚያቋቁማቸውን ተቋማት በተመለከተ ምርጫ ቦርዱን የሚመለከት አይደለም” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡