የትግራይ ክልል የጣስኩት ውሳኔ የለም አለ
የፌዴራል መንግስት ከትግራይ ክልል ጋር ጦርነት ዉስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ጠ/ሚ/ር ዐቢይ መግለጻቸው ይታወቃል
ክልሉ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ችግር ከተፈጠረ ኢ-ሕገመንግስታዊ ያላቸውን አካላት ኃላፊነት ይወስዳሉ ብሏል
የትግራይ ክልል የጣስኩት ውሳኔ የለም አለ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ “በአፋጣኝ እንዲያቆም” በሚል ለጻፈለት ደብዳቤ ምላሽ ሰጠ፡፡
ክልሉ ባለፈው ሳምንት ለተላከለት ደብዳቤ በሰጠው ምላሽ በትግራይ ክልል በኩል የተጣሰ ውሳኔ እንደሌለ አስታውቋል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ ፊርማ ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ/ም ለተጻፈው ደብዳቤ የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባዔ ሩፋኤል ሽፋረ ፊርማ ያረፈበት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ደብዳቤው የትግራይ ክልል ለማካሄድ ያሰበው ምርጫ ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነትን መወጣት እንጂ ከፍላጎት የሚመነጭ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ የትግራይ ክልል በምላሹ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ያስቀመጠላቸውን ሥልጣን አልፈው ነው ደብዳቤውን የላኩት ብሏል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሉ “የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር ስለማሳሰብ” በሚል ርዕስ ከሰሞኑ በጻፈው ባለ ሶስት ገጽ ደብዳቤ “የትግራይ ክልል 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እንዲራዘም የተሰጠውን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ምርጫ ለማካሄድ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አረጋግጫለሁ” በማለት ነበር የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለትግራይ ክልል ልኮ የነበረው፡፡
ክልሉ ዛሬ ለዚህ ደብዳቤ በሰጠው ምላሽ የክልል መንግስት ማቋቋም ሕገ መንግስታዊ መብት ነው ብሏል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሉ የምክር ቤቱን ውሳኔ ካለማክበር ባሻገር ግልጽ የሕገ መንግስት ጥሰት መፈጸሙንም ነው ያስቀመጠው፡፡ ምክር ቤቱ “እንቅስቃሴው ሕገ መንግስቱን ከመቃረን፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ ከመጣልና የፌዴራል ስርዓቱን ከመጉዳትም በላይ የፌዴራል መንግስንቱ ስልጣን ያላከበረ ነው” ቢልም የትግራይ ክልል ግን የሀገሪቱን ሕገ መንግስት አንዳንድ አንቀጾች በመጥቀስ ሕጋዊ ነኝ ብሏል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሉ ሕገ መንግስቱን ማክበር እንዳለበት ገልጾ ይህ ካልሆነ ግን በሀገሪቱ ሕገ መንግስት እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ህጎች የተሰጠውን ስልጣን በመጠቀም እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ሲገልጽ ፣ ትግራይ ክልል በበኩሉ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላ ችግር ቢፈጠር ኢ-ሕገ መንግስታዊ ያላቸው አካላት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ብሏል፡፡
የትግራይ ክልል ለፌደሬሽን ምክር ቤት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ምላሽ ከመስጠቱ አስቀድሞ በርካታ የታጠቁ የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በትናንትናው ዕለት ወታደራዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና ሰልፉ ለምን እንደተደረገ በክልሉ መንግስት በኩል የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በትግራይ ክልል ይደረጋል የተባለው ምርጫ ብዙም እንደማያስጨንቃቸው ነገር ግን በሚደረገው ምርጫ የክልሉ ገዢ ፓርቲ (ሕወኃት) ሥልጣኑን ለሌላ ፓርቲ አሳልፎ ከሰጠ ችግር ይፈጠራል ማለታቸው ይታወሳል፡፡