“ሕወሓት ምርጫ አድርጎ ሥልጣኑን ለአረና ከሰጠ ችግር ይፈጠራል“ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ሕወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ ቦርድ አቋቁሞ ምርጫ ለማካሄድ ወስኗል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ይካሄዳል የተባለው ምርጫ እንዳማያሳስባቸው ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ይካሄዳል የተባለው ምርጫ እንዳማያሳስባቸው ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የፌደሬሽን ምክርቤት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት “ምርጫ 2012” ሲራዘም የሁሉም ክልሎች ስልጣን እንዲራዘም ስለተወሰነ፤ሕወሓት ምርጫ እድርጎ ስልጣኑን ለሌላ ፓርቲ እስካልሰጠ ድረስ እንደማያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቦርድ አቋቁም እየሰራ መሆኑ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ያሉት በትናንትናው እለት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትግራይ ክልል ይደረጋል ስለተባለው ምርጫ ፣ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተፈጥረው ስለነበሩ ችግሮች፣ ሥለ ሀገራዊ መግባባት፣ሥለ ታላቁ የሕዳሴ ግድብና በቀጣይ ዓመት ስለሚካሄደው ምርጫና ስለሌሎች ጉዳዮች ውይይት ባደረጉበት ወቅተ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከሰሞኑ በአርቲስት ኃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ አባሎቻውና አመራሮቻቸው እንደታሰሩባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ የትግራይ ክልል ምርጫ እንደሚደርግ መግለጹን ተከትሎ የፌዴራል መንግስትን አስተያየትና ምላሽ ምን እንደሆነ ማብራሪያ ሲጠይቁ ቀሪዎቹ ደግሞ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የሕግ ማስከበር ችግር እንዳለ አንስተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ከደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥያቄ አንጻር መልስ የሚሰጣቸው ችግሮች እንዳሉና በመንግስት መዋቅር ውስጥ አሉ ያሏቸውን ችግሮችም አንስተዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተደረገው በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ቢሆንም ሰፋ ያለጊዜ የወሰደውና የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ግን በትግራይ ክልል ምርጫ ይደረጋል መባሉን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ምንድን ነው የሚለው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር “የዕድር ምርጫን ወይም የድርጅት ጉባዔን” ምርጫ ብሎ መጥራት እንደሚስቸግር ነው የገለጹት፡፡
ምርጫው በኮሮና ምክንያት ባይራዘም ኖሮ ብልጽግና ምርጫ እንዲደረግ አቋም ይዞ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢበዛ ከዚህ በኋላ ምርጫ ለማድረግ 10 ወራትን ቢፈጅ ነው ብለዋል፡፡በትግራይ ክልል አሁን ያለው እንቅስቃሴን በተመለከተ ክልሉ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡንና ቦርዱ ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ቀሪው ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚመለከተውና እርሳቸውን ግን ብዙም እንደማያስጨንቃቸው ተናግረዋል፡፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ በክልልም በፌዴራልም አሁን ሥልጣን ላይ ያሉ መንግስታት ይቀጥሉ ብሎ መወሰኑን ያስታወሱት ዶ/ር ዐቢይ “ሕወኃት ድራማ ሰርቶ ተመልሶ ነኝ ቢል እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ውሳኔ ነው እየደገመ ያለው እንጅ ምንም ትርጉም የለውም፣ ችግር የሚፈጠረው ግን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አድርጎ ሥልጣኑን ለአረና ከሰጠ ግን ያኔ ግጭት ይፈጠራ“ ብለዋል፡፡ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ አረና ፓርቲ መንግስት መሆን እንደማይችል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫው ተወዳድሮ አረና የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ የሆነ እንደሆነ ከፌዴራል መንግስት ጋር ጸብ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕወሃት “ወረቀትም በትኖ ፣ጉባዔ አካሂዶ ፣የዕድር ስብሰባ አካሂዶ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ተመልሶ ቢመጣ ገንዘብ ፣ጊዜና ጉልበት ከማጥፋት ውጭ ምንም ትርጉም የለውም የሚለውን ድርጅቱና ሕዝቡ ሊገመግመው ይችላል“ ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግስት “ለዚህ ድራማ የሚያወጣው ገንዘብ የለም፤ በድራማው ግን ሕግ የሚጥስ ከሆነና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚያስተላልፍ ከሆነ ጉዳዩን መንግስት የሚመለከተው ጉዳይ ይሆናል“ ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት ግን ምርጫ አደርጋለሁ የሚሉ ሃሎች በተናገሩና ባወሩ ቁጥር ወደ ውጊያ የሚገባ ከሆነ ለሌሎች ጉዳዮች የሚሰጠውን ትኩረት እንደሚሻማና የተጀመሩ ሥራዎችን “ ያዳፍናል“ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ መንግስታት ባህሪ ወደ ውጊያ በተገባ ቁጥር ውጊያ ስላለ ሕዝቡን ዝም በሉ የማለት እንደሆነና ይህም አምባገነንነትን ያመጣል ብለዋል፡፡ የእርሳቸው መንግስትም ወደዚህ ከገባ ይህንን ማለቱ እንደማይቀር እና ይህም ዴሞክራሲን ሊጠፋው እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ጉዳዩን በሰከነ መንገድ መመልክት እንደሚገባ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ብዙም ቀዳሚ አጀንዳ የሚሆን አይደለም ብለዋል፡፡ “የዕድር ስብስብ ነው“ ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ይህ ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነና ከዛ ይልቅ የሀገረ መንግስት ግንባታው ትርክ እንደሚያሳስብ ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ክልል ይደረጋል ስለተባለው ምርጫ ከሰሞኑ ከፋና ቴሌቪዥን ትግርኛ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤልን (ዶ/ር) ሕዝቡ ሊያግዛቸው ይገባል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት ኮሮናን እንደሰበብ ተጠቀመበት እንጂ ከመጀመሪያውም ምርጫውን ለማካሄድ ፍላጎት አልነበረውም ሲል ይከሳል፡፡ የፌደራል መንግስት በበኩሉ ምርጫ ለማካሄድ ጽኑ ፍላጎት ከነበራቸው ፓርቲዎች አንዱ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል፤ይህን ትችትም አይቀበለውም፡፡