ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 500 ወረዳዎችን መለየቱን ኮሚሽኑ ገለጸ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች 218 ቦታዎች መለየታቸው ተገልጿል
ባለፉት ሳምንታት በበርካታ ቦታዎች በተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል
በዘንድሮው ክረምት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡
በቅርቡ በጎፋ በደረሰው የመሬት መንሸራተት በአጠቃላይ 243 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በወላይታ ዞን እና በሲዳማ ክልል በደረሱ ተመሳሳይ አደጋዎች 17 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በግንቦት ወር ኢጋድ እና የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስትቲዩት በተከታታይ ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ሌሎች ሀገራት ከፍተኛ ዝናብ እንደሚጠበቅ አስጠንቅቀው ነበር፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት ኢጋድ ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት የክረምት ወራት በማዕከላዊ እና ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ ፣አብዛኛው ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን እና በኬንያ ጠረፎች መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ ስለሚኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስትቲዩት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና፤ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም እና አዊ ዞኖችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ከፍ ያለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
እስካሁን ባለው የሞት አደጋ በተከሰተባቸው የጎፋ እና ወላይታ ዞኖች እንዲሁም ሲዳማ ክልል ባለፈ በደሴ ከተማ እና በጂማ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተከስተዋል፡፡
አል ዐይን አማረኛ በዘንድሮው አመት ከክረምት ጋር በተገናኝ የጎርፍ እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋ ስጋት ቅድመ ዝግጅት እና በቀጣይ ሊኖሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ምን አይነት እርምጃዎች ተወስደዋል ሲል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ባሳለፍነው አመት ከ79 ሰዎች በላይ በተፈናቀሉበት የኦሞ ዞን ዘንድሮም የአደጋ ስጋት አለ፡፡ የዞኑ መንግስት ኮምንኬሽን መምሪያ ሃላፊ አሸናፊ ጩንጩሌ በሳለፍነው አመት በተከሰተው ጎርፍ የተፈናቀሉ ዜጎች አሁንም በጊዜያው መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ወደ መንደር ውስጥ ገብቶ የነበረውን የኦሞ ወንዝ ሙላት በአፈር ግድብ ወደ ኋላ እንዲሸሽ ማድረግ ቢቻለም ዘንድሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚጥል ከሆነ ግድቡን ጥሶ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ስጋት መኖሩን ነግረውናል፡፡
የወይጦ እና የኦሞ ወንዝ በኦሞራቴ ከተማ እና በሀመር ወረዳ አሁንም ከፍተኛ ስጋት መሆናቸውን ያነሱት ሃላፊው የወንዞችን ሙላት ሊቀንሱ የሚችሉ የውሀ ማፋሰሻዎች በዘላቂነት ለመስራት ከመንግስት እና እርዳታ ድርጅቶች ጋር በትብብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አሸናፊ ከጎርፍ ስጋቱ ባለፈ በዞኑ ተፋናቃዮች በሚገኙባቸው ስፍራዎች የተከሰቱ ውሀ ወለድ በሽታዎች በወረርሽኝ ደረጃ እያደጉ መምጣታቸው በአካባቢው ከጎርፍ እኩል ስጋት መደቀናቸውን ያነሳሉ፡፡
ዳሰነች ፣ ሳላማጎ ፣ እኛጋቶ እና ሀመር ወረዳ የወባ፣ ኩፍኝ እና የኮሌራ በሽታዎች በወረርሽኝ ደረጃ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አካባቢው የአርብቶ አደር አካባቢ እንደመሆኑ የመኖ እጥረት እና የከብቶች በሽታ ተጨማሪ ፈተና መደቀኑን ሰምተናል፡፡
ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ቦታዎች በቦቴ ውሀ ለማቅረብ ጥረት ቢደረግም ተፈናቃዮችን በቋሚነት ማስፈር ካልተቻለ የንጹህ መጠጥ ውሀ ችግር ዘላቂ እንደሚሆን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡
የመሬት መንሸራተት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች
የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ በቀሪ የክረምት ወራቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተት ሊኖር እንደሚችል በትላንትናው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስጠንቅቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ክረምቱ በላኒና (የሙቀት መጠንን በመቀነስ ከፍተኛ ነፋስ እና ሃይል የሚጠቀም የአየር ንብረት ተፅእኖ) ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖር ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በነሐሴና መስከረም ወራቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖር የመሬት መንሸራተት፣ የውሃ መተኛት፣ ጎርፍ፣ የወንዝና የግድቦች ሙላት፣ የሰብል በሽታ፣ የአፈር መሸርሸር እንደሚኖር ተገልጿል።
በደሴ ከተማ፣ በወላይታ፣ ኮይሻና ሌሎችም ቦታዎች ላይ የመሬት መንሸራተት እንደሚከሰት ትንበያው አመላክቷል።
በአዋሽ፣ ተከዜ፣ ባሮ፣ ጣና በለስ፣ ፎገራና ሌሎች አካባቢዎች በወንዞች ሙላት ጎርፍ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
ከሰሞኑ ከተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ምን ያህሎቹን በቅደመ ትንበያ ተለይተው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተላልፎባቸው ነበር ስንል የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን ጠይቀናል፡፡
በኮሚሽኑ የኮምንኬሽን ዳይሬክተር አቶ አታለል አቡሃይ በሰጡን ምላሽ “ሁሉም ቦታዎች ላይ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል መተንበይ አንችልም፤ ነገር ግን በመላ ሀገሪቱ በ500 ወረዳዎች አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ከጂኦስፓሻል እና ከሜትሮሎጂ ኢንስትትዩት ያገኝናቸውን ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ክልሎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ አከፋፍለናል” ብለዋል፡፡
መደበኛ እና ከመደበኛ ከፍ ያለ የዝናብ ስርጭት የሚኖርባቸውን እና ተደጋጋሚ በጎርፍ የሚጠቁ ስፍራዎች በሀገሪቱ ደቡባዊ አጋማሽ ፣ ምስራቅ እና ደቡብ ምዕራብ ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ ሰሜን ምስራቅ ፣ የታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ፣ ተከዜ ፣ የባሮ ወንዝ እና ተፋሰስ አደጋ ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ ከተለዩ ስፍራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ዳይሬክተሩ ኮሚሽኑ የብሄራዊ የጎርፍ አደጋ መከላከል ግብረ ሀይል አቋቋሙ የአደጋ ቅነሳ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና በአደጋ ጊዜ የሚስፈልጉ የሰበአዊ ድጋፎችን ለማድረግ ሃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጅት አድርጓል ብለዋል፡፡
ከክረምት ጋር በተገኛኝ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን መቀነስ ካልሆነ ጭራሽ ማስቀረት የሚቻል ባለመሆኑ በተለያዩ አደጋዎች የሰዎች ህይዎት ማለፉን አቶ አታለል ይናገራሉ፡፡
የ243 ሰዎችን ህይወት የነጠቀው የጎፋው የመሬት መንሸራተት አደጋ በቅድመ ጥንቃቄ መረጃው መሰረት ሰዎችን ከአደጋው ስፍራ ለማዘዋወር እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት መከሰቱንም አንስተዋል፡፡
አክለውም የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የክልል ቢሮዎች የአደጋ ቅነሳን ለማከናወን ዜጎችን ወደ ሌሎች ስፍራ ለማዘዋወር በሚጥሩበት ወቅት ከስፍራው ለመነሳት የሰዎች ፈቃደኛ እና ተባባሪ አለመሆን የአደጋዎችን ጥፋት እያከፋው እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
በጎፋ በተከሰተው አደጋ ከ6000 በላይ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በአሁኑ ወቅት ስራዎች ተጀምረዋል።
በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች ሊከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ አሁን የቅድመ ጥንቃቄ መረጃዎችን ማሰራጨት እና የአደጋ መከላከል ስራዎች እንደሚቀጥሉ አቶ አታለል ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ የአደጋ ተጋላጭነት ሁኔታ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በከተማዋ ከክረምት ጋር በተገናኝ 218 ለአደጋ ተጋላጭ ስፍራዎችን መለየታቸውን አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ይክፈለው ወልደመስቀል ኮሚሽኑ በከተማዋ ጉዳት ያስከትላሉ ተብለው ከተለዩ አስር አደጋዎች መካከል የመሬት መንሸራተት በአራተኛ ላይ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡
የካ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ከተፈጥሯዊ አቀማመጣቸው ጋር በተገናኝ አደጋው ሊከሰትባቸው እንደሚችል ተለይቶ ባለፉት አመታት የችግኝ ተከላ እና የአካባቢ ጥበቃ ሲሰራባቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡
ጎርፍን በተመለከተ ከ11ዱ ክፍለከተሞች ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ከሚባሉ ስፍራዎች መካከል የአቃቂ ቃሊቲ ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና የአዲስ ከተማ ክፍለከተሞች በቀዳሚነት ይገኛሉ፡፡
በሁሉም ክፍለ ከተሞች አደጋ ሊከሰትባቸው ይችላሉ ተብለው ከተለዩት 218 ስፍራዎች በ105ቱ የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መከናዎናቸውን የሚነሱት ኮሚሽነሩ፤
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እና ሌሎች የሴክተር መስርያቤቶችን በማስተባበር የግንብ መጠበቂያ ፣ የውሀ ማፋሰሻዎችን መጠገን እና መቅደድን ጨምሮ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ከሚባሉ ስፍራዎች ነዋሪዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማዘዋወር ስራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡
ከፍተኛ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የአደጋ መከላከል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የሚናገሩት ኮሚሽነሩ ከዚህ ባለፈ በቀጣይ በሚኖሩ የዝናብ ወቅቶች ህብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመዲናዋ የተለያዩ ስፍራዎች በተለይ በጉርድ ሾላ እና ሰሚት አካባቢዎች አስፓልት ላይ የሚተኛው ጎርፍ ለእግረኛ እና ተሸከርካሪ እንቅስቃሴ አደጋች በመሆኑ በችግሩ ዙርያ ምን ታስቧል በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ ዘመናዊ የማፋሰሻ ማስተርፕላን እየተዘጋጀ በመሆኑ ችግሩ በቅርቡ ሊቀረፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡