በጎፋ ዞን በደረሰ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የሟቾች ቀጥር 257 መድረሱ ተገለፀ
በመሬት ናዳ በአደጋው የሟቾች ቁጥር እስከ 500 ሊደስር እንደሚችል ተመድ አስታውቋል
የአካባቢው መልክዕ ምድር ሰዎችን የማፈላለግ ስራው በማሽን እንዳይደገፍ እንቅፋት ፈጥሯል
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባሰለፍነው ሰኞ ጠዋት በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 257 መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ (ኦቻ ) ገለጸ፡፡
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ያስታወቀው ኦቻ በአካባቢው የሚገኙ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ 15ሺህ ሰዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዘዋወር እንቅስቀሴ መጀመሩን ነው ይፋ ያደረገው።
የገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ የሟቾች ቁጥር 229 መድረሱን መናገራቸውን ባሳለፍነው ማክሰኞ የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዘግቦ ነበር።
ዛሬ ኦቻ ያወጣው ሪፖርት የሟቾች ቁጥር በ28 መጨመሩን አመላክቷል። የተጎዱ ሰዎችን የማፈላለግ ስራው በሰዎች ጉልበት በእጅ ቁፋሮ ብቻ ሁኔታዎችን ከባድ ስለማድረጉ ተነግሯል።
አል ዐይን አማረኛ የፍለጋ ስራውን በተመለከተ ከጎፋ ዞን የኮምኒኬሽን ሃላፊ አቶ ካሳሁን ጋር ባደረገው ቆይታ አሁንም በእጅ ቁፋሮ ሰዎችን የማፈላለግ ስራው መቀጠሉን ሰምቷል።
ቁፋሮውን በኤክስ እስካቫተር እና በሌሎችም ማሽኖች ለማድረግ ሀሳቦች ቢኖሩም የአካባቢው መልክዓ ምድር አመች ባለመሆኑ ቁፋሮውን በሰዎች ሀይል ለመቀጠል ተወስኗል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የማፈላለግ ስራውን የሚያግዙ የተለዩ አማራጮችን ለማፈላለግ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል የተካተተበት ግብር ሀይል በጋራ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን ሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ስራዎች መጀመራቸውንም አቶ ካሳሁን ለአል ዐይን አማረኛ ተናግረዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመፈላግ በስፍራው የተገኙ ሰዎች ተጨማሪ ናዳ በመከሰቱ የሟቾች ቁጥር እንዲጨምር እንዳደረገው ተነግሯል።
በነዳው ከተቀበሩ ሰዎች መካከል የጤና ባለሙያዎች ፣ መምህራን እና አርሶ አደሮች የወረዳው ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ሴቶችና ሕፃናት ይገኙበታል ተብሏል።
ከባለፈው ሚያዝያ ጀምሮ በስፍራው ቀደም ብሎ የገባው የክረምት ዝናብ ተጨማሪ ለጎርፍ አደጋዎች መከሰት እና ለበርካቶች መፈናቀል መሆኑን ኦቻ አመላክቷል፡፡ በዚህም እስከ 19 ሺህ ሰዎች የአደጋ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።
በአደጋው 15 ሺህ ሰዎችን በፍጥነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማዘዋወር ስራው በፍጥነት መጀመር እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን ከኒዚህ ውስጥ 5293 እርጉዝ ሴቶች እና 1320 ህጻናት እንደሚገኙበት ኦቻ አስታውቋል።