በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የ18 ሰዎች አስክሬን በፍለጋ እስካሁን አልተገኝም
በአሁኑ ወቅት 10 ሰዎች ከአደጋው ተርፈው ህክምና እየተከታተሉ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተናግረዋል
ርዕሰ መስተዳድሩ አደጋው የደረሰው 88 አባዎራዎችን ከአካባቢው ለማስወጣት እየሰራን ባለንበት ወቅት ነው ብለዋል
ባሳለፍነው ሰኞ በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ እስከ አሁን የ232 ወገኖች ሕይወት ማለፉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ፡፡
ርእሰ መስተዳደሩ ከሰአታት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአደጋው ከሞቱት ሰዎች ባለፈ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ አስር ሰዎች በሳውላ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ከመኖርያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ርዕሰ መሥተዳድሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ አደጋ የሚከሰትባቸውን ቦታዎች ተለይተው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ተላልፎ እንደነበር በመግለጫው ላይ ተመላክቷል፡፡
ይህን ተከትሎም አደጋው በተከሰተበት አካባቢ እና በሌሎች የአደጋ ቀጠናዎች የሚገኙ 88 አባዎራዎችን ወደ ሌሎች ስፍራዎች ለማዘወወር እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት አደጋው ስለመድረሱ ርዕሰ መስተዳደሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
አደጋው በመጀመርያ የተከሰተባቸውን ሁለት ቤተሰቦችን ለመታደግ በስፍራው የተገኙ በአጠቃላይ 232 ሰዎች በናዳው ህይወታቸው ማለፉን ነው ያረጋገጡት
ቀሪ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች የማፈላለጉ ስራ መቀጠሉን ርእሰ መስተዳደሩ የተናገሩ ሲሆን፤ አልአይን አማረኛ ከሰሞኑ ከዞኑ ኮምኒኬሽን ሃላፊ ጋር ባደረገው ቆይታ በናዳው የተዋጡ ሰዎችን የማፈላለግ ስራው በማሽኖች እንዳይደገፍ የአካባቢው መልክአ ምድር እንቅፋት ስለመሆኑ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በአደጋው የ18 ሰዎች አስክሬን በፍለጋ እስካሁን አልተገኝም ፣ ከ6ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ የመሬት ናዳ በሚደርስባቸው ስፍራዎች ላይ ለአደጋ ተጋልጠው ስለሚገኙ ዘላቂ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ርእሰ መስተዳደሩ የክልሉ መንግስት በዘላቂነት ጉዳት የደረሰባቸውን ለመደገፍ ከፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ እስከአሁን በተደረገው ድጋፍ ከ60 ሚሊዮን በላይ በዓይነትና 16 ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ (ኦቻ ) ባሳለፍነው ኃሙስ ባወጣው መግለጫ፤ በመሬት መንሸራተት አደጋው አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 257 መድረሱን መግለጹ ይታወሳል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ያስታወቀው ኦቻ በአካባቢው የሚገኙ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ 15ሺህ ሰዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዘዋወር እንቅስቀሴ መጀመሩን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደ ሀገር በዚህ ክስተት ብሔራዊ ሀዘን ታውጆ መሪር ሀዘኑ የመላው ኢትዮጵያዊያን ሆኖ በማጽናናት የደገፉትን፣ የሀዘን ምልዕክት የላኩ እና ድጋፍ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን እና ዓለም አቀፍ መንግስታት ስላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።