ኮሚሽኑ እስከ ሀምሌ 30 በተቀመጠው ቀነገደብ ሀብታቸውን ሳያስመዘግቡ የቀሩ ሹሞች በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብሏል
ኮሚሽኑ እስከ ሀምሌ 30 በተቀመጠው ቀነገደብ ሀብታቸውን ሳያስመዘግቡ የቀሩ ሹሞች በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብሏል
የፌደራል ስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ስም ዝርዝር በወንጀል ለማስጠየቅ ለፌደራል ፖሊስ በቅርብ ቀናት ውስጥ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳሬክተር መስፍን በላይነህ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት አብዛኞቹ የመንግስት ባለስልጣናት ሀብታቸውን አስመዝግበው ጨርሰዋል፤ ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ያልሆኑትን ባለስልጣናት ሀብት ኮሚሽኑ እያጣራ ነው፡፡
ከፍተኛ ባለስልጣናት እስከ ሰኔ 30 የሀብታቸውን ዝርዝር እንዲያስመዘግቡ ቀነገድብ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፤ የተቀመጠው ቀነገደብ ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሞ ወደ ሀምሌ 30 መራዘሙን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የማስመዝገቢያ ግዜው ወደ ሀምሌ 30 የተራዘመው የአርቲስት ሀጫሉን ሁንዴሳን ግድያን ተከትሎ በተፈጠረው ችግር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገርግን ቀነገደቡ ለሁለተኛ ጊዜ ቢራዘምም፤ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ ባለስልጣናት መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ባለስልጣናቱ በአዋጅ የወጣውን ህግ ባለማክበራቸውና ህግ እንደጣሱ ስለሚቆጠር እንዲጠየቁ ይደረጋል ብለዋል ዳሬክተሩ፡፡
“ስማቸው በግልጽ ተለይቶ ዝርዝር ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በፊት እንደምናደርገው አንዳንድ ተቋማት እያልን አንጠራም፤ የተቋምና የግለሰብ ግልጸኝነት ይለያያል፡፡ ስለሆነም ሀብት ያላስመዘገቡትን በስም ዝርዝር ለይተናል፡፡ በወንጀል እንዲጠየቁ ለፌደራል ፖሊስ የስም ዝርዝራቸውን እንልካለን፡፡ ግልባጭ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ ለህዝብ ተወካዮችና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ይላካል” ዳሬክተሩ አንደተናገሩት፡፡
ዳሬክተሩ አቶ መስፍን ሀብታቸውን ማስመዝገብ ያለባቸው የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ሚኒስትሮችን፤ ሚኒስትር ዲኤታዎችን፤ የመንግስት ልማት ድርጅቶችን የቦርድ ሰብሳቢዎችን፣ ምክትል ሰብሳቢዎችን፤ ኮሚሽነሮችንና ምክትል ኮሚሸነሮችን ያካትታል ብለዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚያስገድደው አዋጅ ቁ.668/2002 ሆኖ በ2002ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጸድቆ ነበር፡፡ በዚህ አዋድ መሰረት የፌደራል የመንግስት ሰራተኞች፤ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የመንግስት ሰራተኞችንና የህዝብ ተመራጮች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ይደረጋል፡፡
ዳሬክተሩ እንደገጹት የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ህጉ ቢጠይቅም፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቅድሚያ ማስመዝገብ እንደሚገባቸው ገልጿል፡፡
የከፍተኛ ባለስልጣናትን ሀብት መመዝገብ ለምን ያስፈልጋል?
አቶ መስፍን እንደገለጹት የመንግስት ሀብት በሹመኞች እጅ ስለሚወድቅ ሙስናን ለመከላከል ሲባል የከፍተኛ ባለስልጣናትን ሀብት መመዝገብ አስፈላጊ የሚያደርግ አዋጅ አንዲወጣ ሆኗል፡፡
ዳሬክተሩ አንድ ሹም ከመሾሙ በፊት የነበረው ሀብት ምን እንደነበረና ከተሾመ በኋላ ያገኘውን ሀብት ይገመግማል፤ ምን ይዞ መጣ፤ ምን ይዞ ወጣ የሚለው ይታያል ብለዋል፡፡
የከፍተኛ መንግስት ባለስልጣናት ሀብት መመዝገብ ያስፈለገው የመንግስትን የግልጸኝትና ተጠያቂነት አሰራር ለመዘርጋት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላልና ለህዝብ አገልግሎት የተሰጠ ኃላፊነትን ለግል ጥቅም እንዳይውል ለማድረግ ነው ብለዋል፡፤
ሀብት ማስመዝገብ ለህዝብና ለመንግስት ታማኝነት ማሳያ ነው ያሉት ዳሬክተሩ ኮሚሽኑ የመዘገበውን መረጃ ለማንኛውም ለጠየቀ አካል መስጠትና የተመዘገበውን ሀብት እውነተኛነት የመመርመር ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
“ኮሚሽኑ የምርመራ ስራ ይሰራል፤ ባለስልጣኑ ያስመዘገበው ሀብትና በተጨባጭ ያለውን ያገናዝባል፡፡ በዚህ ሂደት ሌላ ሀብት ከተገኘ ባለስልጣኑ የማስረዳት ግዴታ አለበት” ብለዋል ዳሬክተሩ፡፡
ዳሬክተሩ እንደገለጹት ባለስልጣናቱ በተሾሙ በ45 ቀናት ውስጥ ሀብታቸውን ያስመዘግባሉ፤ በየሁለት አመቱ ምዝገባውን አሳድሰው ወቅታዊ መረጃ ይይዛሉ፡፡