ልዩልዩ
የደብረብርሃን ምክትል ከንቲባ በሙስና ተጠርጥረው ታሰሩ
ጉዳዩ ገና በመጣራት ላይ ነው ያለው የከተማው ፖሊስ ወደፊት ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚሰጥ አስታውቋል
የከተማው የመሬት አስተዳደር አመራር አካላትን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች መታሰራቸውም ተሰምቷል
የደብረብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ በሙስና ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደብረብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ታዬ ወልደ ጊዮርጊስ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው ከከተማ የመሬት የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተናገሩት ኮማንደር ታየ ሌሎች 4 ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮማንደሩ “ጉዳዩ ገና በመጣራት ላይ ነው ገና የጋራም አላደረግነው የእያንዳንዳቸው ወንጀልም ይለያያል“ ያሉ ሲሆን የተጠርጣሪዎቹን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
የጉዳዩን ዝርዝር ሁኔታ በቀጣይ እንደሚያሳውቁም ነው የገለጹት፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ግን ከምክትል ከንቲባው በተጨማሪ የከተማው የመሬት ልማት ቡድን መሪው አቶ ደምሴ ተፈረደኝ እና አቶ ኃይሉ ሽፈራው እንዲሁም ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘግቧል፡፡