የ64 ዓመቱ አብዱላህ ሳምቢ ግን የታሰርኩት በፖለቲካ ስጋት ምክንያት እንጂ በሙስና አይደለም ብለዋል
ኮሞሮስ የቀድሞ ፕሬዝዳንቷን በእድሜ ልክ እስራት ቀጣች፡፡
ደቡብ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኮሞሮስ የቀድሞ ፕሬዝዳንቷ የሆኑትን አህመድ አብዱላህ ሳምቢ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወስናለች፡፡
ከፈረንጆቹ 2006 እስከ 2011 ድረስ ኮሞሮስን በፕሬዝዳንትነት የመሩት አብዱላህ ሳምቢ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው የሀገሪቱን ፓስፖርት ለውጭ ሀገራት ዜጎች ሸጠዋል በሚል ነው፡፡
አብዱላህ ሳምቢ ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩ ሲሆን ከስድስት ወር በፊት ጀምሮ ደግሞ የኮሞሮስ ዜግነትን ለሚፈልጉ የውጭ ሀገራት ሰዎች ፓስፖርት ሸጠዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የ64 ዓመቱ ሳምቢ በመንግስት የቀረበባቸውን ክስ የተቃወሙ ሲሆን እኔ የታሰርኩት አሁን ስልጣን ላይ ላሉት ፕሬዝዳንት ጋዛሊ ኤል ኦትማኒ መንግስት በስጋትነት ስለተፈረጅኩ ነው ሲሉ ለሀገሪቱ ፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡
የተከሰሱበትን ወንጀል ተቃውመው ለፍርድ ቤቱ ከተናገሩ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት አልሄድም ያሉት ሳምቢ በሌሉበት ጉዳያቸው ታይቶ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ተገልጿል፡፡
የኮሞሮስ መንግስት አቃቢ ህግ እንዳሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሳምቢ የሀገሪቱን ፓስፖርት እንደ ሸቀጥ ለውጭ ሀገራት ዜጎች ቸርችረዋል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ህዝብ ብዛት ያላት ኮሞሮስ በውሃ የተከበበች ሲሆን ሞሮኒ ደግሞ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ነች፡፡
ከአፍሪካ ካሉ ድሃ ሀገራት ተርታ የምትመደበው ኮሞሮስ ዜጎቿ በወባ በሽታ በብዛት የሚጠቁ ሲሆን በፈረንጆቹ 1975 ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ ወጥታለች፡፡