በቶማስ ሳንካራ ግድያ የተከሰሱት የቡርኪና ፋሶ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው
ቶማስ ሳንካራ የቡርኪናፋሶ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት ነበሩ
ቶማስ ሳንካራ ከ34 ዓመት በፊት ነበር የተገደሉት
በቶማስ ሳንካራ ግድያ የተከሰሱት የቡርኪና ፋሶ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ብሌስ ኮምፓውሬ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ተነገለፀ።
የቡርኪናፋሶ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት የነበሩት ቶማስ ሳንካራ ከ34 ዓመት በፊት ነበር የተገደሉት።
ቡርኪና ፋሶ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ የቀድሞ ፕሬዝዳንቷን ገዳዮች ወደ ፍርድ አደባባይ ልታመጣ ሂደት መጀመሯን አስታወቀች።
የሚወዳትን ሀገሩን እየመራ የነበረው ቶማስ ሳንካራ አሰቃቂ በተባለ ግድያ ህይወቱ ቢያልፍም በበርካታ አፍሪካውያንና የአፍሪካ ወዳጆች ስሙ ጎልቶ ይነሳል።
በአራት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ተዓምር የሚያስብሉ ስራዎችን መስራቱንም በርካቶች ይመሰክራሉ።
በአውሮፓውያኑ 1987 በቅርብ ወዳጁ ብሌስ ካምፓውሬ አስተባበሪነት በተመራ መፈንቅለ መንግስት የሳካራ ሕይወትና ስልጣን ተጠናቆ ነበር።
አፍሪካዊው ቼ ጉቬራ እየተባለ የሚጠራው ሳንካራ እንዲገደል አሲረዋል በሚል የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ችሎት ቀርበው የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በግድያ ወንጀሉ ዙሪያ ፍርድ መስጠቱን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ ዘግቧል።
በዚህም መሰረት የቀድሞው የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት ብሌስ ኮምፓውሬ እና ረዳቶቻቸው የነበሩት ጊልበርት ዴንድሬ እና ካፋዶ ሂያቺንቴ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የቶማስ ሳንካራ ባለቤት ከ 34 ዓመታት በኋላ የሳንካራ ገዳዮች የፍርድ ሂደት መጀመር ስትጠብቀው የነበረ ሁኔታ እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግራለች።
የቀድሞው የቡርኪናፋሶ ፕሬዝዳንት የደህንነት ኃላፊ ካፋንዶ አንዱ የግድያ ተጠርጣሪ መሆኑ ቀደም ብሎ መነገሩ ይታወሳል።
የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትና የቶማስ ሳንካራ የቅርብ ወዳጅ ብሌስ ካምፓውሬ ዋነኛ የግድያው ተጠርጣሪ መሆናቸው ቀደም ብሎ የተዘገበ ቢሆንም ግለሰቡ ግን በዚህ ግድያ ላይ እጃቸው እንደሌለበት ሲናገሩም ቆይተዋል።
ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ 100 ጋዜጠኞች የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ፍርድ ሂደቱን ለመከታተል በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኡጋዱጉ መገኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቶማስ ሳንካራ ባለ ራዕይ እና እውነተኛ አፍሪካዊ መሪ በሚል የሚወደስ ሲሆን፤ በፕሬዝዳንትነት ዘመኑ በብስክሌት በመሄድ የመንግስትንና የሀገርን ወጭ በመቀነሱ ስሙ ይነሳል።
ለመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተብለው የተዘጋጁ መርሴድስ መኪኖችን በርካሽ ተሸከርካሪዎች በመቀየርም የሀገርን ወጭ እንደቀነሱ ይጠቀሳል።