የ5 ኪሎሜትር የሩጫ ውድድር ያልጨረሱ ሰራተኞቹን ያባረረው ኩባንያ
የቻይናው ኩባንያ በ30 ደቂቃ ውስጥ 5 ኪሎሜትር ሩጠው ያልጨረሱ ሰራተኞችን ጠንካራ የስራ ብርታት የላቸውም ብሎ አስናብቷል
ኩባንያው ክስ ቀርቦበት ላባረራቸው ሰራተኞች ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበታል
በቻይና ጂያንግሱ ግዛት ሱዡ ከተማ ሰራተኞቹን በሩጫ ፈትኖ ያሰናበተው ኩባንያ መነጋገሪያ ሆኗል።
ሊዮ ስሙ ባልተጠቀሰው የማምረቻ ፋብሪካ በተቀጠረ በቀናት ልዩነት ውስጥ ከስራው መሰናበቱን ተከትሎ ያቀረበው ክስ ነው ዜናው እንዲሰራጭ ያደረገው።
ሊዮ በፋብሪካው መካኒክ ሆኖ ለመቀጠር የጽሁፍ እና የተግባር ፈተናውን ከወሰደና የህክምና ወጪውን ራሱ ችሎ የምርመራ ውጤቱን አቅርቦ በተቀጠረ በቀናት ልዩነት ሌላ ፈተና እንዳለ ተነገረው።
ፈተናውን ማለፍ ካልቻለም እንደሚባረር አዳዲሶቹ ባልደረቦቹ አስጠነቀቁት።
ይሁን እንጂ አዲሱ ፈተና በ30 ደቂቃ ውስጥ 5 ኪሎሜትሮችን በሩጫ ማጠናቀቅ እንደሆነ አልጠበቀም።
ይባስ ብሎ በፈተናው ቀን የሙቀት መጠኑ 40 ዲግሪ ሴልሺየስ ሆኖ ተፈጥሮም ከኩባንያው ስራ አስፈጻሚ ተደርባ ፈተናውን አከበደችበት።
ሊዮ በከረረችው ጸሃይ 800 ሜትር ገደማ እንደሮጠ አልቻለም፤ አቋርጦት ወደ ቢሮ ያመራል። በማግስቱ ወደ ቢሮ ሲመለስም ከስራ መሰናበቱ ተነግሮታል።
ሊዮ 5 ኪሎሜትር በ30 ደቂቃ ውስጥ ሩጦ ያልጨረሰ ሰራተኛ ብቁ አይደለምና ከእኛ ጋር አይቀጥልም ካለው ፋብሪካ ሲባረር እንዲሁ አልተመለከም፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል።
ኩባንያው አስቀድሞ ስለአካል ብቃት ፈተናው አላሳወቀኝም፤ ከተቀጠርኩ በኋላ ለአዲስ ፈተና መቀመጤና በዚህም መሰናበቴ ተገቢ አይደለም የሚል ክስም አቅርቧል።
የሱዡ ከተማ ፍርድ ቤትም ኩባንያው ለሊዮ የ1 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፍል መወሰኑ ተገልጿል።