ማደያውን የዘረፉት ሰዎች በፖሊስ ሲያዙ ዝረፉት ተብለን ማለታቸውን ፖሊስ ገልጿል
በጊዜ ወደ ቤቱ ለመግባት ሲል የነዳጅ ማደያውን ያዘረፈው ሰራተኛ አነጋጋሪ ሆኗል።
ኢሳያስ ጆንስ የተሰኘው ግለሰብ በሀገረ አሜሪካ ኦክላሃማ ግዛት ባለ የነዳጅ ማደያ የሽያጭ ሰራተኛ ነው።
ከሰሞኑ እሰከ ምሽት ድረስ ቆይቶ የመስራት ግዴታ እያለበት ድካም ሲሰማው በጊዜ ወደ ቤቱ መሄድ ይፈልጋል። ለዚህ እቅዱ ይረዳው ዘንድም አንድ ዘራፊ ሰው በመመልመል የነዳጅ ማደያው እንዲዘረፍ አድርጓል ተብሏል።
ይህ ሰራተኛ ማደያው ላይ በተፈጸመው ዘረፋ ምክንያትም ድንጋጤ ያለበት እና ስራውን መስራት አልቻልኩም በሚል በጊዜ ወደ ቤቱ ማምራቱ ተገልጿል።
የኦክላሃማ ፖሊስም ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቶ ሽጉጥ ተጠቅሞ በነዳጅ ማደያው ላይ ዝርፊያውን የፈጸመውን ግለሰብ ማንነት እንደደረሰበት እና በቁጥጥር ስራ ያውለዋል።
ስቴቨን ጆንስ የተሰኘው ይህ ዘራፊ በፖሊስ ምርመራ ወቅት ዝርፊያውን መፈጸሙን አምኖ ነገር ግን ዝረፍ ተብሎ በተነገረው መሰረት ማድረጉን ለፖሊስ ይናገራል።
ነዳጅ ማደያውን ማን ነው ዝረፍ ያለህ በሚል ከፖሊስ ለቀረበለትም ጥያቄ አልያ ሎክ የተሰኘች እንስት መሆኗን የሰማው ፖሊስ ይህችን ተባባሪም በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
በፖሊስ የተያዘችው አልያ ሎክ የነዳጅ ማደያው ሰራተኛ የሆነው ኢሳያስ ጓደኛዋ እንደሆነ፣ ከባድ ድካም እንዳለበት እና ማደያውን የሚዘርፍ ሰው ብታዘጋጅለት ለእረፍት ወደ ቤቱ እንደሚሄድ በጠየቃት መሰረት እንደተባበረችው ለፖሊስ ተናግራለች።
የኦክላሃማ ፖሊስም በነዳጅ ማደያው ላይ የተቀነባበረ ዝርፊያ እንዲፈጸምበት ያስተባበሩ እና የፈጸሙ በሚል ቅጣት እንዲጣልባቸው ክስ መመስረቱ ተገልጿል።