በየቀኑ 3 ኪሎ ሜትር ለሚሮጡ ሰራኞቹ የጉርሻ ገንዘብ የሚሰጠው ኩባንያ
ሰራተኞቹ በወር ውስጥ በሮጡት ኪሎ ሜትር መጠን የወር ደመወዛቸው ላይ ተጨማሪ ጉርሻ ያገኛሉ
አዲሱ የጉርሻ ክፍያ አሰራር ትልቅ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን ኩባንያ አስታውቋል
የቻይና ኩባንያ በየቀኑ ቢያንስ 3 ኪሎ ሜትር የሚሮጡ ሰራተኞቹ በደመወዛቸው ላይ ተጨማሪ የጉርሻ (ቦነስ) ገንዘብ እንደሚያገኙ አስታወቀ።
ኩባንያው የዓመቱ መጨረሻ ላይ ለሰራተኞቹ የሚታሰበውን የጉርሻ (ቦነስ) ክፍያን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለማበረታታት በተዘጋጀ ሌላ እቅድ የቀየረ ሲሆን፤ በዚህም በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሰሩ ሰራተኞች የቦነስ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በቻይና ጓንግዶንግ ግዛት የሚገኘው ጓንግዶንግ ዶንግፖ የወረቀት ፋብሪካ በዓመቱ መጨረሻ በአፈጻም ላይ ተሰምርቶ የሚሰጠውን የጉርሻ (ቦነስ) ክፍያን በአትሌቲክስ ስፖርት አፈጻም በመተካቱ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ኩባንያው በ100 ሰራተኞቹ መካከል ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለማስተዋወቅ ባለመው አዲሱ ስርዓት ምን ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ በመመልከት የጉርሸ ገንዘብ (ቦነስ) ለመስጠት መወሰኑንም አስታውቋል።
ለምሳሌ አንድ ሰራተኛ በወር 50 ኪሎ ሜትር የሚሮጥ ከሆነ ሙሉ ወርሃዊ ደመቀዙን በተጨማሪ በጉርሻ (ቦነስ) ለማግኘት ብቁ ይሆናል።
በወር ውስጥ 40 ኪሎ ሜትር ለሚሮጥ 60 በመቶ ጉርሻ (ቦነስ)፤ በወር 30 ኪሎ ሜትር ለሚሮጥ ሰራተኛ ደግሞ የደመወዙ 30 በመቶ በጉርሻ ይሰጠዋል ተብሏል።
ሰራተኛው በአንድ ወር ውስጥ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ መሮጡን ካረጋገጠ ተጨማሪ 30 በመቶ ጉርሻ (ቦነስ) እንደሚያገኝም ኩባንያው አስታውቋል።
እያንዳንዱ የኩባንያው ሰራተኛ የሚሮጠው ርቀት በስልከቸው ላይ በተጫነ መተግባሪያ አማካኝነት ክትትል የሚደረግበትና የሚመዘገብ መሆኑም ተነግሯል።
ዶንግፖ የወረቀት ሥራ አስኪያጅ ሊን ዚዮንግ “የእኔ ንግድ ዘላቂ ሊሆን የሚችለው ሠራተኞቼ ጤናማ ከሆኑ ብቻ ነው” ብለዋል።
አዲሱ የጉርሻ ክፍያ አሰራር ትልቅ ስኬት ያስመዘገበ ሲሆን ራሱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድናቂ የሆነው ዶንግፖ ወረቀት ሥራ አስኪያጅ ሊን ዚዮንግ ሁሉም ሰራተኞች ሙሉ ጉርሻ ለማግኘት ብቁ መሆናቸውን ተናግሯል።