ሰራተኞቹ እንዲለቁ ለማበረታታት ቢሮውን ወደ ተራራማ ስፍራ ያዛወረው የቻይና ኩባንያ
የማስታወቂያ ኩባንያው ቢሮውን ወደ ገጠራማና ለስራ የማይመች ስፍራ የቀየረው ሰራተኞቹ በፈቃዳቸው ለቀው ካሳ እንዳይጠይቁት በማሰብ ነው ተብሏል
ኩባንያው ሰራተኞቹ ከለቀቁ ከቀናት በኋላ ወደ ቀድሞ ቢሮው መመለሱም የቀድሞ ሰራተኞቹን አበሳጭቷል
የቻይናው የማስታወቂያ ኩባንያ ሰራተኞቹ ከስራ እንዲለቁ ለማበረታታት የተጠቀመው ስልት የቀድሞ ሰራተኞቹን አስቆጥቷል።
ሺያን በተባለችው ከተማ በምቹ እና በከተማ መሀል ሲሰራ የቆየው ኩባንያ ቢሮውን ወደ ገጠራማ እና ለስራ ምንም ምቾት ወደሌለው ስፍራ ቀይሯል።
ቻንግ የተባለ የቀድሞው የኩባንያው ሰራተኛ እንደሚለው ሺንሊንግ በተሰኘ ተራራ መሃል የሚገኝ ሲሆን የህዝብ ትራንስፖርት ሊገኝበት የማይችል ስፍራ ነው።
የግል መኪና የሌላቸው ሰዎች ወደ አዲሱ ቢሮ ለመድረስ በጥቂቱ ሁለት ስአት ይወስድባቸዋል የሚለው ቻንግ፥ “መኪና የሌለን እኔና ባልደረቦቼ በሶስት ስአት አንድ ጊዜ የምትመጣ አውቶብስ መጠበቅና ሶስት ኪሎሜትር የሚረዝም ተራራን በእግር መጓዝ ግድ ይለን ነበር” ሲል ያስታውሳል።
“በታክሲ ወደ አዲሱ ቢሮ ለመጓዝ እስከ 8 ዶላር ክፍያ እንጠየቃለን፤ ይሁን እንጂ ይህን ክፍያ ኩባንያው ለመክፈል አልፈለገም” በማለትም ምሬቱን ይገልጻል።
አዲሱ ቢሮ መጸዳጃ ቤት የሌለው በመሆኑም ሴቶች ባለደረቦቻቸው ወደ ቅርብ መንደር በመጓዝ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶችን ለመጠቀም መገደዳቸውንም በማከል።
የትራንስፖርት ችግሩ ከውሾች ጩኸት ጋር ተዳምሮ ምንም ለስራ ምቹ እንዳልሆነ ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢቀርብም የኩባንያው አስተዳደር መፍትሄ ሊፈልግ አልቻለም ባይ ነው ቻንግ።
በዚህም ምክንያት ከ20 ሰራተኞች ውስጥ 14ቱ የስራ መልቀቂያ አስገብተው ስራቸውን መልቀቃቸውን ያወሳል።
ይሁን እንጂ ሰራተኞቹ በለቀቁ በቀናት ልዩነት የማስታወቂያ ኩባንያው ተራራ ላይ የነበረውን ቢሮ ለቆ ዳግም ወደቀድሞው ቢሮ መመለሱና ሰራተኞችን ለመቅጠር ማስታወቂያ መለጠፉ ነው ቻንግን ጨምሮ የቀድሞ ሰራተኞቹን ቅር ያሰኘው።
ኩባንያው ሆን ብሎ ወደማይመች ቢሮ አስገብቶ ተማረን በፈቃዳችን እንድንወጣ ያደረገው ካሳ ላለመክፈል ማለታቸውንና ክስ እንደሚመሰርቱ ማሳወቃቸውን ተከትሎም ስሙ ያልተጠቀሰው ኩባንያ ምላሽ ሰጥቷል።
“በመሃል ሺያን የቢሮ ኪራይ ውድ ስለሆነና የቀድሞ ቢሯችን እየታደሰ ስለነበር ነው ወደ ተራራማው ቢሮ የተዛወርነው፤ የቢሮ ቅያሬው ሰራተኞችን ያለካሳ ከማሰናበት ጋር ግንኙነት” የለውም ሲል መቃወሙንም ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት አስነብቧል።
ይሁን እንጂ የቀድሞው ሰራተኞች ኩባንያው ጉዳዩን አሳንሶ ለማየት መሞከሩን ተቃውመው ወደ አዲሱ ቢሮ ስንዛወር ቢያንስ ለአንድ አመት በዚያ እንደምንሰራ ተነግሮናል፤ በአጭር ጊዜ እንደሚመለስ ብናውቅ ስራችን አንለቅም ነበር የሚል ቅሬታ አሰምተዋል።
ጉዳዩ በቻይና ማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን፥ የኩባንያው የቢሮ ለውጥ አንድምታ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ነው።
በአሰሪ እና ሰራተኛ ውል የስራ ቦታ የሚገኝበት አካባቢ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፤ ኩባንያው ቢሮውን ያለሰራተኞቹ ይሁንታ ከቀየረም የህግ ጥሰት ፈጽሟል የሚሉ የህግ ባለሙያዎችም የቀድሞው ሰራተኞች ክስ ቢመሰርቱ ካሳ ሊያገኙ እንደሚችሉ መግለጻቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።