የፈረንሳዩ የቴሌኮም ኩባንያ ለ20 አመታት ሳልሰራ ደመወዝ እየተከፈለኝ ነው ባለች ሰራተኛው ተከሷል
ሰራተኛዋ ለስራ አመቺ ሁኔታ ሳይፈጥርልኝና ይህ ነው የሚባል ስራ ሳይሰጠኝ ለ20 አመታት ደመወዝ ብቻ መክፈሉ ሞራሌን ጎድቶታል ብላለች
ኩባንያው ግን የአካል ጉዳት ያለባት ሰራተኛዋ ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲፈጠርላት የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን በመግለጽ ተከላክሏል
ያለምንም ስራ ለ20 አመታት ደመወዝ ተከፍሎኛል ያለች ፈረንሳዊት ቀጣሪዋን ከሳለች።
ላውረንስ ቫን ዋስንሆቭ ከፈረንጆቹ 1993 ጀምሮ በኋላ ላይ ኦሬንጅ የጠቀለለው ፍራንስ ቴሌኮም ሰራተኛ ናት።
የቀድሞው ቀጣሪዋ ፍራንስ ቴሌኮም በከፊል ሰውነቷ እንደማይታዘዛት እና የሚጥል ህመም እንዳለባት በመገንዘብ ከጤናዋ ጋር የተገናዘበ አመቺ ስራና የስራ ቦታ አመቻችቶላት እንደነበር ትናገራለች።
እስከ ፈረንጆቹ 2002 በጸሃፊነት እና የሰው ሃይል ክፍል ስትሰራ የቆየችው ቫን ዋስንሆቭ ወደሌላ የፈረንሳይ ከተማ ዝውውር ጠይቃ ፈቃድ ካገኘች በኋላ ግን ይህ ነው የሚባል ስራ እንደሌላት ነው የምትገልጸው።
የተዘዋወረችበት ቢሮ ለስራ ምቹ እንዳልሆነ ደጋግማ ብትጠይቅም ፍራንስ ቴሌኮምን የገዛው ግዙፉ የቴሌኮም ኩባንያ ኦሬንጅ ስራዋን የምትቀጥልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳልቻለ ታክላለች።
ይልቁንም ምንም አይነት ስራ ሳይሰጣት ባለፉት 20 አመታት ደወመዟን ሳያቋርጥ መክፈልን መርጧል።
ቫን ዋስንሆቭ ሳትሰራ የሚከፈላት ደመወዝ እና በአካል ጉዳቷ ምክንያት ደረሰብኝ የምትለውን “የሞራል ጥቃትና መድልኦ” በተመለከተ ለተለያዩ ተቋማት ብታሳውቅም እስካሁን መፍትሄ ባለማግኘቱ ኦሬንጅ የቴሌኮም ኩባንያንና አራት ስራ አስኪያጆቹን ከሳለች።
“የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ጋር መስራት በማህበረሰቡ ውስጥ ስፍራ እንደተሰጣቸው ያሳያል፤ እውቅና እና ማህበራዊ ትስስሩንም ያጠብቃል” የሚሉት የቫን ዋስንሆቭ ጠበቃ፥ ደንበኛቸው ስራዋን ትለቃለች በሚል ተስፋ ለ20 አመታት ሁሉም ተዘጋግቶባት መቆየቷን ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ጋዜጣ ላ ዲፔሽ ክስ የቀረበበትን ኦሬንጅ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረ ሲሆን ኩባንያው ቫን ዋስንሆቭ በተሻለ የስራ ከባቢ እንድትሰራ የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን ገልጿል።
ተቋሙ ሰራተኛዋ በተደጋጋሚ የህመም ፈቃድ እየወሰደች የስራ ገበታዋ ላይ ባትገኝም ያለችበትን የጤና ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ደመወዟንና ሌሎች ድጋፎችን ያለማቋረጥ እየሰጠ መሆኑንም ነው ያነሳው።