በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በድጋሚ ግጭት ተከሰተ
በሁለቱ ዞኖች ከአንድ ወር በፊት በተነሳ ግጭት ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት ስለማለፉ መገለጹ ይታወሳል
በግጭቱ ምክንያት ከአዲስ አበባ- ደሴ -መቀሌ የሚያስኬደው ዋና መንገድ ትራንስፖርት ተቋርጧል
ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ሀይል እና መከላከያ ሰራዊት ተሰማርቶ ለጊዜው ግጭቱ ቆሞ ነበር።
ይሁንና በአጣዬ ከተማ ከትናንት በስቲያ አንድ መኖሪያ ቤት መቃጠሉን መነሻ በማድረግ በአካባቢው ውጥረት ነግሶ ከዛሬ ሌሊት አንስቶ ግጭቱ ተከስቶ የሰዎች ህይወት በማለፍ ላይ መሆኑን ለአል አይን ዜና ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ትናንት ጀምሮ በኤፍራታ እና ግድም ቀወት እና ወረዳ እና በአንጻኪያ ወረዳ ስር ባሉ ካራቆሬ ቆሪሜዳ ማጀቴ መስኖ ካብሰራምባ ገተም ውሃ ኩሪብሪ ዋጮ እና ዘንቦ ቀበሌዎች ግጭት ተከስቶባቸዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ በአጣዬ ከተማ ከባድ የተኩስ ልውውጥ በመደረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ችግሩ በአካባቢው ካለው ልዩ ሀይል እና መከላከያ ሰራዊት አቅም በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ወደነዚህ ቀበሌዎች በመግባት ጥቃት በመፈጸም ላይ ያሉት ታጣቂዎቹ የያዙት የጦር መሳሪያ ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ ታጣቂዎቹ ወደ መከላከያ ሰራዊት ላይም እየተኮሱ መሆኑንም ገናዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ጥቃቱ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያትም ነዋሪዎቹ አሁን ላይ መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ ሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች እና ከተሞች በመሸሽ ላይ መሆናቸውንም አክለው ተናግረዋል።
በግጭቱ ምክንያት ከአዲስ አበባ- ደሴ -መቀሌ የሚያስኬደው ዋና መንገድ ትራንስፖርት መቋረጡንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ካሉ ከተሞች ወደ ከሚሴ አጣዬ ኮምቦልቻ ደሴ እና መቀሌ ለመጓዝ መንገድ የጀመሩ የጭነት እና የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ሸዋሮቢት ላይ መቆማቸው ተገልጿል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ደህንነት መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ መኮንን በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ቢሆንም ያሉበት ሁኔታ መረጃ መስጠት የማያስችል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል።
አል ዐይን ዜና ከአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብያደርግም አልተሳካም።
ሁለቱ ዞኖች ከአንድ ወር በፊት በተነሳ ግጭት ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባወጣው ሪፖርት መግለጹ ይታወሳል።