እጩ ፕሬዘዳንቱ ህመም ሲበረታባቸው ወደ ፈረንሳይ በመጓዝ ላይ እያሉ በአውሮፕላን ውስጥ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል
ኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዘዳንታዊ ምርጫዋን በማካሄድ ላይ ስትሆን በዚህ ምርጫ ላይ እጩ ፕሬዘዳነት የነበሩት ብሪስ ኮሌላ ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ አፍሪካ ዘግባል።
እጩ ተወዳዳሪው ሰሞኑን የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በማካሄድ ላይ እንደነበሩ ዘገባው ጠቁሟል።ይሁንና ዛሬ ሌሊት ህመሙ ሲበረታባቸው ወደ ፈረንሳይ በመጓዝ ላይ እያሉ በአውሮፕላኑ ውስጥ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የ61 ዓመቱ ኮሌላ ከሌሎች 5 እጩዎች ጋር ለፕሬዘዳንትነት በመወዳደር ላይ የነበሩ ሲሆን የምርጫው ውጤት ሳይታወቅ ህይወታቸው አልፏል።
ላለፉት 36 ዓመታት የሀገሪቱን በትረ ስልጣን ጨብጠው የቆዩት ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ኑጉሶ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ተጠብቋል።
በማእከላዊ አፍሪካ የምትገኘውና በዘይት አምራችነቷ የምትታወቀው ኮንጎ ሪፐብሊክ ቀጣይ መሪዋን ለመምረጥ በዛሬው እለት የምርጫ ጣብያዎቿን ለመራጮች ክፍት አድረጋለች፡፡
የ77 ዓመት አዛውንቱ ፕሬዝዳንት ሳሱ በ1979 ወደ ስልጣን የመጡ በ 1992 የኮንጎ የመጀመሪያ የመድብለ ፓርቲ ምርጫን ተሸነፈው ኃላፊነታቸውን ለቀው ነበር።
ይሁንና መሸነፋቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በ 1997 እንደገና የፕሬዝዳንትነቱን በትረ ስልጣን መጨበጥ ችለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ወደ መሪነት ከተመለሱ በኋላ ህገ-መንግስት ማሻሻያ በማድረግና የስልጣን ገደብን በማራዘም እስካሁን ድረስ ሀገሪቱን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡