በኮንጎ ሪፓብሊክ ለሚካሄደው ፕሬዝዳንት ምርጫ የሀገሪቱ የፀጥታ ሀይሎች ቀድመው ድምፅ ሰጡ
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ፤ የፀጥታ ሀይሎቹ ድምፅ የሚቆጠረው ከሲቪል መራጮች ጋር እንደመሆኑ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም ብሏል
12 ሺ የሀገሪቱ ወታደሮች እና ፖሊሶች ድምፅ ሰጥተዋል
ቀድሞ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ በመካከለኛው አፍሪካ ምዕራባዊ ዳርቻ በምትገኘው ሀገረ ኮንጎ ታሪክ ያልተለመደ ነውም ተብሎለታል፡፡
በዚህም የፀጥታ ሀይሎቹ በመጪው ረቡዕ ከሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቀደም ብልው፤ በዶሊሴ ከተማ ድምፅ መስጠት መጀመራቸውን ነው የኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡ 12 ሺ የሀገሪቱ ወታደሮች እና ፖሊሶች ድምፅ መስጠታቸውንም ጭምር፡፡
የፀጥታ ሀይሎቹ ቀደም ብለው ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉ ታዲያ በምርጫው ቀን በየ ምርጫ ጣቢያዎች የሚኖረውን ድባብ በብቃትና በተጠናከረ ሁኔታ እንዲከታተሉ የሚያስችል እንደሆነ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በመግለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡
መንግስት እንዲህ ቢልም ግን አብዛኞቹ ተቀናቃኝ ሀይሎች ሂደቱ ካሁኑ እየተጭበረበረ እንደሆነና ለፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ንጉሶን ያደላ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የ “ራስ-ለ-ቦል (ፌዴሬሽን) ንቅናቄ”ው በርትራንድ ሜኒየር፤ የመራጮቹ ዝርዝር “ወታደሮችን ከሲቪሎች የለየ” እንዳልሆነ በመግለፅ “የወታደሮቹ ስም በወታደሮች እና ሲቪል መራጮች ዝርዝር ውስጥ እንደመኖሩ ፤ሁለት ጊዜ ሊመርጡ ይችላሉ ብለን እንሰጋለን” ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ፡ የፀጥታ ሀይሎቹ ድምፅ የሚቆጠረው ከሲቪል መራጮች ጋር እንደመሆኑ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም ሲል ተደምጠዋል፡፡
ላለፉት 36 ዓመታት ኮንጎ ሪፓብሊክን የመሩት፤ የ77 ዓመት የእድሜ ባለጸጋው ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ንጉሶን አሁን ላይ ማትያስ ድዞን እና ጉይ ብራይስ ፓርፋይትን የመሳሰሉ የቀድሞ ሚኒሰትሮቻቸውን ጨምሮ በስድስት ተፎካካሪዎች የሚፈተኑ ይሆናል፡፡