በፕሬዚዳንቱ ግድያ ተፈርዶባቸው ላለፉት 20 ዓመታት እስር ላይ የነበሩት ሁሉ የይቅርታው አካል ናቸው
በቀድሞው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ላውረንት ካቢላ ግድያ ወንጀል የተፈረደባቸው ሁለት ሰዎች ይቅርታ እንዲደረግላቸው ተወሰነ፡፡
ካቢላ በጠባቂያቸው መገደላቸው ቢታወቅም ፣ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ኮሎኔል ኢዲ ካፔንድና ጆርጅስ ለታ ግን በግድያው እጃቸው አለበት ተብለው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ግለሰቦቹ የተፈረደባቸውን የሞት ፍርድ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ቺሲኬዲ ባለፈው ሰኔ ማስቀረታቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ይቅርታ ተድርጎላቸዋል፡፡
ይቅርታው ከአባታቸው ግድያ በኋላ ፕሬዚዳንት በነበሩት ጆሴፍ ካቢላ እና በአሁኑ ፕሬዚዳንት ቺሲኬዲ መካከል መጥፎ ግንኙነት ሊፈጥር እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ጆሴፍ ካቢላ ከአባታቸው ላውረንት ካቢላ መገደል በኋላ በአውሮፓውያኑ 2001 ሥልጣን ይዘው በ2018 ነው በምርጫ የተሸነፉት፡፡ ፕሬዚዳንት ቺሲኬዲ ምርጫውን ቢያሸንፉም ጆሴፍ ካቢላ የለቀቁት ግን ከጀርባ በተደረገ የፖለቲካ ንግግር ነው ተብሏል፡፡
ጆሴፍ ካቢላ አሁንም በሀገሪቱ ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸው ይነገራል፡፡ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት እንዳለው በፕሬዚዳንቱ ግድያ ተፈርዶባቸው ላለፉት 20 ዓመታት እስር ላይ ለነበሩት ሁሉ ይቅርታው ካለፈው ታህሳስ 31 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ኮ/ል ኢዲ ካፔንድ ግድያውን አቀናብሯል የሚል ክስ ቀርቦበት ቢታሰርም ይህንን እንዳልፈጸመ ተናግሯል፡፡
የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የፕሬስ ኃላፊ እንዳሉት በግድያው ወንጀለኛ የተደረጉት ኮሎኔል ኢዲ ካፔንድ እና ከእርሱ ጋር የተወነጀሉት ከዚህ ይቅርታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ኮሎኔል ኢዲ ካፔንድ የላውረንት ካቢላ ቀኝ እጅ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በግድያው ግን አቀነባባሪ ተብሎ ከአጠቃላይ የጸጥታ ቡድኑ ጋር ነበር የታሰረው፡፡ የደህነነት ኃላፊው ጆርጅስ ለታም በግድያው ተጠርጥሮ እስር ቤት እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን ሁለቱም ግድያው ላይ እጃቸው እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ወንጀለኛ ተብለው እስር ላይ የቆዩት ግለሰቦች ይቅርታ የተደረገላቸው የፕሬዚዳንት ቺሲኬዲ ፓርቲ በፓርላማው ብዙ ወንበር ካለው የጆሴፍ ካቢላ ፓርቲ ጋር የነበረው ጥምረት ካበቃ በኋላ ነው፡፡ አሁን ላይ ፕሬዚዳንቱ የእርሳቸው ፓርቲ በፓርላማ አብላጫ ወንበር እንዲኖረው የሚጣመራቸውን ፓርቲ እየፈለጉ ነው፡፡