የፕሬዘዳንት ዴኒስ ሳሱ ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበሩት ብራይስ ኮሌላስ በኮሮና ምክንያት ከምርጫው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል
ባሳለፍነው እሁድ በኮንጎ ሪፐብሊክ በተካሄደ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሀገሪቱን ላለፉት 36 ዓመታት የመሩት ሳሱ ንጉሶ መመረጣቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ፕሬዘዳንቱ በዚህ ምርጫ ላይ 88 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ተገልጿል።
በዘንድሮው ምርጫ ላይ የፕሬዘዳንት ዴኒስ ሳሱ ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበሩት ብራይስ ኮሌላስ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከምርጫው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
እጩ ተወዳዳሪው የምርጫ ቅስቀሳ አድርገው ህመም ሲበረታባቸው ወደ ፈረንሳይ በመጓዝ ላይ እያሉ በአውሮፕላን ውስጥ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የ61 ዓመቱ ኮሌላ ከሌሎች 5 እጩዎች ጋር ለፕሬዘዳንትነት በመወዳደር ላይ የነበሩ ሲሆን የምርጫው ውጤት ሳይታወቅ ህይወታቸው አልፏል።
ኮንጎ ሪፐብሊክ በማእከላዊ አፍሪካ የምትገኝ ሲሆን በዘይት አምራችነቷ ትታወቃለች።
የ77 ዓመት አዛውንቱ ፕሬዝዳንት ሳሱ በ1979 ወደ ስልጣን የመጡ በ 1992 የኮንጎ የመጀመሪያ የመድብለ ፓርቲ ምርጫን ተሸነፈው ኃላፊነታቸውን ለቀው ነበር።
ይሁንና መሸነፋቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በ 1997 እንደገና የፕሬዝዳንትነቱን በትረ ስልጣን መጨበጥ ችለዋል።
ፕሬዘዳንቱ ወደ መሪነት ከተመለሱ በኋላ ህገ-መንግስት ማሻሻያ በማድረግና የስልጣን ገደብን በማራዘም እስካሁን ድረስ ሀገሪቱን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡