የኒጀር ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ማካሄዳቸውን አወጁ
ወታደሮቹ በብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ስራ ማቆማቸውንና የሀገሪቱ ድንበር መዘጋቱን ገልጸዋል
የመንግስታቱ ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ አለማቀፍ ተቋማትና ሀገራት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱን እየተቃወሙ ነው
ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙምን በትናንትናው እለት ያፈኑት የኒጀር ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ማካሄዳቸውን ገለጹ።
ኮሎኔል ማጅ አማዱ አብድራማን ከ9 ወታደሮች ጋር በመሆን በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ነው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ያወጁት።
የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ አስተዳደር በየጊዜው እያሽቆለቆለ መሄዱንም ለመንግስት ግልበጣው በምክንያትነት አንስተዋል።
የሀገሪቱ ህገመንግስት ለጊዜው አይሰራም ያሉት ኮሎኔል ማጅ አብድራማን፥ ሁሉም የመንግስት ተቋማት የጸጥታ ሁኔታው እስኪስተካከል ድረስ ስራ እንዲያቆሙ መወሰኑንም በመግለጫቸው አብራርተዋል።
የኒጀር የየብስ ድንበርም ሆነ የአየር ክልል መዘጋቱን በመጥቀስም “የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ” አሳስበዋል።
የኒጀር ወታደሮች ለሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ታዛዥ እንደሚሆኑም በማንሳት።
ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙም ትናንት በወታደሮች መከበባቸው ከተገለጸ ወዲህ በመዲናዋ ኒያሚ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ እንደማይገኝ አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ ወታደሮቹ ፕሬዝዳንቱ እንዲለቀቁ የድጋፍ ሰልፍ ባደረጉ ኒጀራዊያን ላይ ሲተኩሱ እንደነበር ነው የተገለጸው።
የአፍሪካ ህብረት እና የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) የመንግስት ግልበጣውን የተቃወሙ ሲሆን፥ የቤኒን ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎን ለማሸማገል ኒያሚ ገብተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም መፈንቅለ መንግስቱን “በጥብቅ” ተቃውመው ፕሬዝዳንት ባዙምን ለማስለቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ኒጀር በፈረንጆቹ 1960 ከፈረንሳይ ነጻነቷን ካወጀች በኋላ አራት የተሳኩ የመንግስት ግልበጣዎችን አስተናግዳለች።
ጎረቤቶቿ ማሊ እና ቡርኪናፋሶም መፈንቅለ መንግስት ባካሄዱ ወታደራዊ አዛዦች እየተመሩ ነው።