የኒጀር መፈንቅለ መንግስት ደጋፊዎች “ረጅም እድሜ ለፑቲን” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል
የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ዋግነር አዛዥ ፕሪጎዥን የኒጀርን መፈንቅለ መንግሥት ማወደሳቸው ይታወሳል
ደጋፊዎቹ ሩሲያንና መሪዋን ሲያወድሱ የቀድሞ የኒጀር ቀኝ ገዢ ፈረንሳይ ውድመትን የሚመኙ መፈክሮች አሰምተዋል
በኒጀር ባሳለፍነው ሳምንት የተፈፀመውን መፈንቅለ መንግስት የደገፉ የሀገሪቱ ዜጎች ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፎች ላይ ሩሲያን የሚያወድሱ መፈክሮችን ሲያሰሙ ተስተውሏል።
በቅጽል ስሟ የዩራኒየም ምድር በመባል እምትታወቀው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር ከሰሞኑ መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባታል።
የፕሬዝዳንቱ ጠባቂዎች ፕሬዝዳንት መሀመድ ባዙም በቤተ መንግስታቸው እንዳሉ እንዳይንቀሳቀሱ ታግተዋል።
ጠባቂዎቹ ከእገታው በኋላ በፕሬዝዳንት ባዙም የሚመራው መንግሥት መፍረሱን እና ጀነራል ቲያኒ የሀገሪቱ ሙሪ መሆናቸውን በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ የተለያዩ የድጋፍ እና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ሲሆን፤ በትናትናው እለትም በሺዎች የሚቆጠሩ የመፈንቅለ መንግስቱ ደጋፊዎች ጫና እያደረገች ነው በሏት የቀድሞ የኒጀር ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ኤምባሲ ፊትለፊት ተሰብስበው ቁጣቸውን ገልጸዋል።
አንዳንድ ተቃዋሚዎች በኒጀር የፈረንሳይ ኤምባሲ ታፔላዎችን በመሰባበር ከረገጡ በኋላ በሩሲያ እና በኒጀር ባንዲራ በስፍራው ተክተዋል።
በሰልፈኞቹ መካከል “ረጅም እድሜ ለፑቲን፣ ሩሲያ ለዘላለም ትኑር” የሚሉ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን፤ ውድመት ለፈረንሳይ የሚሉ ድምጾችም ተሰምተዋል።
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር አዛዥ የሆኑት የቨግኒ ፕሪጎዚን መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ የኒጀትን ወታደሮች ማድነቃቸው ይታወሳል።
የቨግኒ በድምጽ ባሰራጨው መግለጫ "የኒጀር ወታደሮች ያደረጉት ነገር ህዝብ በቅኝ ገዢዎች ላይ እያደረጉት ያለን ትግል ማገዝ ነው" ብለዋል።
ይሁን እንጂ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም ሀገራ መንግስታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኒጀር የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም ላይ ይገኛሉ።
የአፍሪካ ህብረት የኒጀር ጁንታ በ15 ቀናት ውስጥ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ባዙምን ወደ ስልጣናቸው እንዲመልስ ያሳሰበ ሲሆን፤ ይህን ተፈጻሚ ካልሆነ ግን የመንግስት ግልበጣውን ባደረጉት ወታደራዊ መሪዎች ላይ “ጠንካራ ማዕቀብ” እንደሚጥል ነው ያስጠነቀቀው።
ለፕሬዝዳንት ባዙም ድጋፋቸውን የገለጹት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትም የመንግስት ግልበጣውን ባደረጉት ወታደራዊ መሪዎች ላይ ማዕቀብ ለመጣል መዘጋጀታቸውን ዩሮ ኒውስ አስነብቧል።