የትራምፕ ደጋፊዎች ወደ ኮንግረስ አዳራሽ ሰብረው መግባታቸውን ተከትሎ 4 ሰዎች ተገደሉ
በአመጹ ስብሰባው ቢስተጓጎልም ኮንግረሱ የትራምፕ ቡድን በ 5 ግዛቶች ያቀረበውን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል
ፕሬዝዳን ትራምፕ ባቀረቡላቸው ጥሪ ነው ደጋፊዎቻቸው ለተቃውሞ ወደ ኮንግረሱ በማምራት ያመጹት
ትናንት ምሽት የትራምፕ ደጋፊዎች ፣ ካፒቶል ሂል በመባል የሚታወቀውን በዋሺንግተን የሚገኝ የሀገሪቱ መንግሥት መቀመጫ ሰብረው በመግባት ፣ የአሜሪካ ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
ካፒቶል ሂል የአሜሪካ ኮንግረስ ፣ ሴኔቱ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚገኙበት ታሪካዊ ህንጻ ነው፡፡
የአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ውጤት ለማጽደቅ በጋራ በመወያየት ላይ እያሉ ነበር የትራምፕ ደጋፊዎች ታሪካዊውን ህንጻ ሰብረው የገቡት፡፡ የትራምፕን መሸነፍ ተቃውመው ኮንግረሱን ለመረበሽ ወደ ካፒቶል ያመሩት ሰልፈኞቹ በህንጻው ላይ በመንጠላጠል ፣ መስኮቶችን እና በሮችን በመስበር ወደ ውስጥ ዘልቀው መግባት ችለዋል፡፡ ደጋፊዎቹ የትራምፕን ጥሪ ተከትሎ ነው ስብሰባውን ለመበጥበጥ የገቡት፡፡
አመጹ በርትቶ ሰልፈኞቹ ዘልቀው ሲገቡ ፣ የካፒቶል ሂል ፖሊሶች ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስን እና የኮንግረሱን አባላት ለደህንነታቸው ሲባል ወደ ድብቅ ስፍራ ወስደው ሸሽገዋቸዋል፡፡
በቀውስ የተሞላው የምሽንቱ ትዕይንት መቆም የቻለው ፣ አመጹ ከተጀመረ ከ 4 ሰዓታት በኋላ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች ወደ ስፍራው አምርተው በተኩስ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነው፡፡ በዚህም ሂደት 4 ሰዎች ሲገደሉ 14 ፖሊሶች መቁሰላቸውን የማስንግተን ዲሲ ፖሊስ ኃላፊ ሮበርት ኮንቴ ገልጸዋል፡፡ አንዲት ሴት በህንጻው ውስጥ ስትገደል ሌላ አንድ ሴት እና ሁለት ወንዶች ከህንጻው ውጭ መገደላቸውንም ነው ያብራሩት፡፡ ህንጻው ውስጥ የተገደለችው ሴት የቀድሞ የሀገሪቱ አየር ኃይል አባል እንደነበረች የአሜሪካ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ግለሰቧ የምርጫውን ውጤት በመቃወም ከትራምፕ ደጋፊዎች ጋር አብራ ወደ ህንጻው ዘልቃ የገባች ናት፡፡
በትራምፕ ጥሪ በዋሺንግተን የተፈጸመውን ድርጊት በመቃወም የፕሬዝዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት ምክትል አማካሪ ማቲው ፖቲንገር እንዲሁም ሁለት የቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ራሳቸውን ከኃላፊነት አንስተዋል፡፡ ሌሎች በርካታ ባለሥልጣናትም በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ይጠበቃል፡፡
ማቲው ፖቲንገር
“በርካታ ሰዎች ለማመጽ እና ውድመት ለማስከተል የጦር መሳሪያ በመታጠቅ እና ሌሎች ኬሚካሎችን በመያዝ ነው ወደ ዋሺንግተን የገቡት” ያሉት የከተማዋ ከንቲባ ሙሪየል ቦውዘር ለ15 ቀናት የአስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል፡፡
ያም ሆነ ይህ ኮንግረሱ በትራምፕ እና በደጋፊዎቻቸው ጥያቄ የተነሳባቸውን የጆርጂያ ፣ ኔቫዳ ፣ ሚሺጋን ፣ አሪዞና እና ፔንሲልቫኒያ ውጤቶችን በማጽደቅ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡