የዩኤኢ ፕሬዚዳንት ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት እና መሃመድ ቢን ዛይድ ጆ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት ብለዋል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ክስ ለመመስረት ተዘጋጅተዋል
የሌሎች ሀገራት መሪዎችም የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እያስተላለፉ ነው
የዩኤኢ ፕሬዚዳንት ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት እና መሃመድ ቢን ዛይድ ጆ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት ብለዋል
ፕሬዝዳንት ክቡር ሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጆ ባይደን የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በቀጣይነት ለሚኖራቸው ስራም ስኬትን ተመኝተውላቸዋል፡፡
ሼህ ካሊፋ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ፣ ሁለቱ ሀገራት እና ህዝቦቻቸውያላቸውን ስትራቴጂካዊ እና ታሪካዊ ግንኙነት አድንቀዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ካሊፋ በተጨማሪም ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሀገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ግንኙነቶች ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላትም ነው የገለጹት፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዥ ክቡር ሼህ መሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም እና የአቡዳቢ ዘውዳዊ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼህ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንም እንዲሁ 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ለተመረጡት ጆ ባይደን ተመሳሳይ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡
የዴሞክራቶቹ እጩ ጆ ባይደን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን በማሸነፍ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ አርባ ስድስተኛው ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡
በእስካሁኑ ውጤት መሠረት ባይዴን 24 ግዛቶችን ያሸነፈ ሲሆን በዚህም 290 የውክልና ድምጽ መሰብሰባቸውን ኤፒ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ሲኤንኤን እና ሌሎች አንዳንድ ሚዲያዎች ደግሞ 279 ድምጽ ስለማግኘታቸው ነው የዘገቡት፡፡ ያም ሆነ ይህ ለአሸናፊነት ከሚያበቃቸው 270 ድምጽ በላይ ማግኘታቸው ተረጋግጧል፡፡
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የዓለም ሀገራት ለባይደን እና ለምክትላቸው ካማላ ሀሪስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ መሪዎች መካከል ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትራምፕንም አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ከተማ መሆኗን እውቅና ከመስጠት ጀምሮ ሀገሪቱ ከዩኤኢ ፣ ከባህሬን እና ከሱዳን የዓረብ ሀገራት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ እንድትደርስ ማደራደር ችለዋል፡፡
አሁን በምርጫው የተሸነፉት ትራምፕ ታዲያ ሽንፈታቸውን ለመቀበል እስካሁን አሻፈረኝ እንዳሉ ናቸው፡፡ የምርጫው አሸናፊ እኔ ነኝ የሚሉት ትራምፕ ፣ በነገው እለት የድምጽ ቆጠራው ተጭበርብሯል ባሉባቸው ግዛቶች ክስ ለመመስረትም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡