የኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት ወጣቶች እንዲሰደዱ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል ተባለ
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን የሚገኙባቸው ናቸው
በኤርትራ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ ምንም የመሻሻል ምልክት እንዳላሳየ ተመድ በሪፖርቱ ገልጿል
በኤርትራ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ አሳሳቢና ምንም አይነት የመሻሻል ምልክት ያላሳየ መሆኑ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክትል ከፍተኛ ኮሚሽነር ናዳ አል-ናሺፍ ተናገሩ፡፡
ናዳ አል-ናሺፍ በ52ኛው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት ከሆነ ኤርትራ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚፈጸምባት ሀገር ሆና እንደቀጠለች ነው ብለዋል፡፡
ኤርትራ አሁንም ድረስ የዘፈቀደ እና ኢ-ሰብአዊ የእስር ሁኔታዎች ያሉባት፣ ሰዎች ደብዛቸው እንዲጠፋ የሚደረግባት፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ የማይቻልባት፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፎች መብቶችን የሚገደቡባት ናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች ለአስርት አመታት ታስረው የሚገኙባት ናት ብለዋል ምክትል ከፍተኛ ኮሚሽነሯ በሪፖርታቸው፡፡
በተለይም የትግራይን ግጭት ተከትሎ የኤርትራ ወጣቶች የጊዜ ገደቡ ለማይታወቅ ብሄራዊ አገልግሎት በገፍ እያታፈሱ ነው ያሉት ናዳ አል-ናሺፍ፤ ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ እስከ እስር የሚደርስ ቅጣት ይበየናል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በኤርትራ በግዳጅ የሚሰጠው ገደብ አልባው ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት በርካታ ወጣቶች ሀገሪቱን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የ2022 መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ከኤርትራ የሸሹ ከ160,000 በላይ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ከ130,000 በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ እና በሱዳን ይገኛሉ፡፡
ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ያለው ድርጅቱ ሀገራቸው ጥለው ከተሰደዱት አብዛኞቹ ከ18 እስከ 49 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብሏል፡፡
አሁን ላይ ሁኔታው አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ ሀገራቸውን ጥለው የወጡትን ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑ ነው ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክትል ከፍተኛ ኮሚሽነር ናዳ አል-ናሺፍ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ትክክል እንዳልሆነ ድርጊቱን የሚፈጽሙ መንግስታት ወቅሰዋል፡፡
በተያያዘ ኤርትራ ብሄራዊ አገልግሎቷን ከአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ግዴታዎች ጋር እንድታስማማ ሲሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል ናዳ አል-ናሺፍ፡፡
ኤርትራ ካለፉት በርካታ አመታት ጀምሮ እየተካሄደ ላለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃ አለመውሰዷ እጅግ እንደሚያሳዝናቸውም ገልጸዋል፡፡