የሩሲያው ከፍተኛ ዲፕሎማት እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ያነሷቸው አንኳር ጉደዮች ምንድን ናቸው?
ኤርትራ በዩክሬን ጉዳይ ሩሲያን ያወገዘው የመጋቢት 2022 የተመድ ውሳኔን የተቃወመች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ነበረች
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ የዩክሬን ጦርነት የምዕራባውያን “የተሳሳተ ፖሊሲ” ውጤት ነው ብለዋል
ለይፋዊ ስራ ጉብኝት ሃሙስ እለት ኤርትራ የገቡት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በተለያዩ አንጓር ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገ/መስቀል የላቭሮቭ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ውይይቶች “በዩክሬን ስላለው ጦርነት ተለዋዋጭነት፣ በማዕድን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጎልበት ላይ ያኮሩ ነበሩ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
በውይይቱ ዓለምን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረገው የምዕራባውያን ጥረት እውን የማይሆን ህልም መሆኑ ያነሱት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ፤ “ዓለምን አደጋ ውስጥ ከቶ የቆየውን የአገዛዘ ታሪክ ለመመከት የተባበረ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
የዩክሬን ጦርነት ዓለምን በበላይነት ለመምራት የሚደረግ የምዕራባውያን "የተሳሳተ ፖሊሲ” ውጤት ነው ሲሉም ተችተዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ፤ የዩክሬን ጦርነት አሜሪካ በምትመራው የምዐረባውያን ቡድን እና ሩሲያ መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው ሲሉ መናገራቸው የሻባይት መረጃ ያመለክታል፡፡
ጀርመን እና ፈረንሳይ እንደፈረንጆቹ ከ2024 አንስቶ ለጦርነት ሲዘጋጁ ነበር ያሉት ላቭሮቭ "ሩስያ የወሰደችው የሰላም አማራጭ ከስትራቴጂያዊ ፍላጎታቸው ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ጦርነቱን ይበልጥ እያባባሱት ይገኛሉ" ሲሉም ከሰዋል፡፡
ክፍተኛ ዲፕሎማቱ ከኤርትራ ጋር ስላለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ሲናገሩም፤ ሞስኮ በበርካታ ዘርፎች ከአስመራ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላት አንስተዋል፡፡
በማዕድን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ትምህርት እና ጤና ሩሲያ ከኤርትራ ጋር በትብብር መስራት የምትችልባቸው መስኮች መሆናቸው በመጥቀስ፡፡
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው ፤ ኤርትራ ለተጠቀሱት የትብብር መስኮች ቅድሚያ በመስጠት ለሁለትዮሽ የኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መጎልበት ትሰራለች ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ክፍተኛ ዲፕሎማቱ፤ ከሀምሌ 26 እስከ 29 ቀን 2023 በሴንት ፒተርስበርግ በሚካሄደውና መሪዎች በሚሳተፉበት ሁለተኛው የሩሲያ- አፍሪካ ኢኮኖሚ ፎረም ፕሬዝዳነት ኢሳያስ እንዲተፉም ግብዣ አቅርበውላቸዋል ሲል ኤሪ-ቲቪ ዘግቧል፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ከኤርትራው አቻቸው ዑስማን ሳልሕ ፣ የፕሬዝዳንት አማካሪው የማነ ገብረኣብ እና የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል ጋር በመሆነ በአስመራ የሚገኘውን የፑሽኪን ሐወልት መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ የምዕራባውያን ጫና የደረሰባት ሩሲያ የአፍሪካን ድጋፍ ለማግኘት የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በማድረግ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡
ላቭሮቭ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እያደረጉት ባለው ጉብኝት ደቡብ አፍሪካን፣ ኢስዋቲኒን ፣ አንጎላን እንዲሁም አሁን ላይ ኤርትራን የመጎብኘታቸው ሚስጥር ይህ እንደሆነም ይታመናል፡፡
የተባበሩት መንግስታት መጋቢት 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ዘመቻ በማውገዝ እንድትወጣ በሚል ባሳለፈው የውሳኔ ኃሳብ ኤርትራ ውሳኔውን የተቃወመች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር እንደነበርች የሚታወስ ነው፡፡
እናም የከፍተኛ ዲፕለማቱ የአሁኑ ጉብኝት ከዚህ ታሪካዊ አቋምና አጋርነት የተነሳ ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ሳይንስ ሊሂቃን ይገልጻሉ፡፡
በተመሳሳይ ሩሲያ ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ የሚያነሳቸውን ክሶች ስትቃወም የቆየች ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡