ኢትዮጵያ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የከሰሰችውን ኤርትራዊ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት ቀጣች
ተከሳሹ ሦስት ግለሰቦችን ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ድንበር ለማሻገር እያንዳንዳቸው 700 የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍሉት አድርጓል የሚል ክስ አቅርቦ እንደነበር ሚኒስቴሩ ገልጿል
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ተከሳሽ በቀረቡበት ሦስት ክሶች በሰው መነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል
የኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር በህወጥ የሰዎች ዝውውር ተከሶ የነበረው ኤርትራዊ ግለሰብ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ በእስራት በቀጣቱን አስታውቋል።
መሀመድ አህመድ የተባለው ኤርትራዊ በፈጸመው ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ105 ሽህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተበየነበት።
ኤርትራዊ ዜግነት ያለው እና የመኖሪያ አድራሻው አዲስ አበባ ከተማ የሆነው ግለሰብ በፈጸመው ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ሦስት ተደራራቢ ክሶች መስርቶ ክርክሩን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ተከሳሽ በሦስቱም ክሶች በሰው መነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን ድንጋጌ በመተላለፍ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው፡፡
ፍትህ ሚኒስቴር እንደገለጸው ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ሳላህ ዑመር አህመድ የተባለውን እና በወንጀል ድርጊቱ ለሞት የተዳረገውን ግለሰብ ቀኑ በውል ባልታወቀበት ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ሌሎች ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ግዛት ወደ ሱዳን ድንበር ለማሻገር እያንዳንዳቸው 700 የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍሉት አድርጓል።
የተረከቡት ግለሰቦችም ስፍራውን መለየት ባልተቻለ ቦታ ሲደርሱ ተከሳሽ የእሱ ሰዎች ባለመሆናቸው እንዲያመልጡ እንደነገራቸው ታውቋል።
ተከሳሽ በፈፀመው ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ሶስት ተደራራቢ ክሶች እንደተመሰረቱበት የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ ተመላክቷል፡፡