“ከሽንፈት አመድ ውስጥ ሳይሆን፤ የአሸናፊነትን አቧራ አራግፎ የሚነሳ የማገገሚያ ዕቅድ ያስፈልገናል”- ፕ/ር መንግስቱ
የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰሩ “በመምረጥ ላይ ያተኮረ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች የለየ እርምጃ ይታደገናል”ም ብለዋል
በጦርነቱ የተጎዳው ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ምን ይደረግ?
በኢትዮጵያ 14 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት አሁን አሁን መልኩን እየቀየረ ይመስላል፡፡
በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራዎችን መፈጸምና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ዘልቆ መግባት መቆጣጠር ጭምር ችለው የነበሩት የህወሓት ኃይሎች አሁን ላይ ይዘዋቸው የነበሩ ቦታዎችን ለቀው በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡
የአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ዞኖችም ነጻ ወጥተዋል፡፡አንዳንድ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ነጻ መውጣታቸውንና ዋናው የወልድያ መቀሌ ጎዳና ተቆርጦ በቁጥጥር ስር መዋሉ መገለጹም ይታወሳል፡፡
መንግስት በህወሓት ተይዘው የነበሩትን ደሴና ከምቦልቻ ከተሞችን ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ
ለመፈናቀል ተዳርገው የነበሩ በርካቶችም ወደየመኖሪያ ቀዬዎቻቸው በመመለስ ላይ ናቸው፡፡
ሆኖም በየአካባቢዎቹ ያለው ውድመት ቀላል አይደለም፡፡ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል የግብርና ምርቶች እና ተቋማት ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፡፡
የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴው ከመቀዛቀዝም አልፎ ቆሞ ነበር ለማለትም ይቻላል፡፡ አሁንም ቢሆን ዳግም ሊያንቀሳቅሰውና ሊያነቃቃው የሚችልን አካል ይፈልጋል፡፡
አል ዐይን አማርኛም በጦርነቱ ምክንያት የተቀዛቀዘው ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንዴት ነው ሊነቃቃ እና ዳግም ሊያንሰራራ የሚችለው? ፤ ምን ያህልስ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል? ሲል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን (EEA)ን ጠይቋል፡፡
የወደመው ኢኮኖሚ በምን ያህል ጊዜ ሊያገግምና ሊያንሰራራ እንደሚችል “በውል ለመለየት ጥናት ቢያስፈልግም በጦርነት በደቀቁ ሃገራት እንደምናየው ረጅም ዓመታት ፈጅቶባቸዋል” የሚሉት የአሶሴሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰሩ መንግስቱ ከተማ “የእኛም ቀላል አይሆንም” ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
ከእንዲህ ዐይነቱ ድቀት ለመውጣት ራሱን የቻለ የማገገሚያ እቅድ (ማርሻል ፕላን) እንደሚያስፈልግም ነው ፕ/ር መንግስቱ የተናገሩት፡፡
ለዚህም ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የማገገሚያ ዕቅድ አዘጋጅታ ያደረገችውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
ልዩነቱ ሌሎቹ እነ ሊቢያ እና አፍጋኒስታንን የመሳሰሉ ሃገራት ጭምር ከጦርነት ለማገገም የሄዱባቸው መንገዶች “ከሽንፈት አመድ ውስጥ የምናንሰራራበት ብለው ከድቀት የሚነሳ የማገገሚያ እቅድ መንደፋቸው” እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
“የእኛ የሚለየው ምናልባት ከሽንፈት አመድ ውስጥ የሚነሳ ላይሆን፤ የአሸናፊነትን አቧራ አራግፎ በመነሳት ሊሆን ይችላል” ሲሉም ያስቀምጣሉ የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰሩ፡፡
በቁርጠኝነት ከተሰራና ጥሩ የማንሰራሪያ ዕቅድ ከተተገበረ አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ “ወደ ነበርንበት ወደተሻለም የኢኮኖሚ ደረጃ ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎች ይታዩኛል” ሲሉም ነው የሚናገሩት፡፡
ራሱን የቻለ የማገገሚያ እቅድ ያስፈልገዋል መንግስት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር በኩል እየሰራበት ያለ ይመስለኛል ሲሉም ገልጸዋል፤ በአጭር እና በረጅም ጊዜ መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ በመጠቆም፡፡
ህወሓት ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በሚገኙ የቱሪዝም ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን መንግስት አስታወቀ
በአጭር ጊዜ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ያጡ ወገኖችን መደገፍ ምንም ጊዜ የሚሰጠው ነገር አይሆንም፡፡ መሰረተልማቶችን መጠገንና ወደቦታቸው መመለስ፤ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ለይደር የሚተዉም አይደሉም እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፡፡ ፡፡
በአጠቃላይ ግን ጦርነቱ ያደረሰው ጉዳት ከባድ እና ለማንሰራራት ሊወጣ የሚችለውም ወጪ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም የሁሉንም ርብርብ ከመጠየቅም በላይ ያለውን ሃብት አብቃቅቶ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
በጦርነቱ ዲፕሎማሲው ጭምር ተጎድቷል፡፡ ከሃገራት ጋር ያለው የንግድ ግንኙነት ስለዳሸቀም የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ በጣም ትንሽ ነው፡፡
ይህ ማለት እንደ ፕ/ር መንግስቱ ገለጻ ከውጭ ለማስገባት የሚፈለጉ እቃዎች እንደልብ አይገቡም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የሚገቡትን (ኢምፖርት) የግድ መምረጥ እና ሌሎች የውጭ ንግድ አማራጮችን በሌሎች ሃገራት ማፈላለግ ያስፈልጋል፡፡
ከዚያ ውጭ ጦርነቱን በቶሎ ቋጭቶ የሰላሙን ሁኔታ ከማረጋገጥ ጎን ለጎን መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ የሚፈልጉ አካላትን መተማመን ከፍ ማድረግና መገንባት፤ ብድርን ጨምሮ የተለያዩ ድጎማዎችን በማድረግ ምቹና ሳቢ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ የታጡትን ምርቶች፣ የምርት ግብዓቶች ለማቅረብ መረባረብም ያሻል፡፡
ሁሉም ዜጋ ከችግሩ እንድንወጣ መረባረብና ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መስራት አለበት የጦርነቱን መልካም ጎኖች መጠቀምም ያስፈልጋል፡፡