በኮፕ28 ከማቀዝቀዣዎች የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ለመቀነስ የፈረሙ ሀገራት ከ60 በላይ ደርሰዋል
ሀገራቱ በ2050 ከማቀዝቀዣ ቁሳቁሶች የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ከባለፈው አመት በ68 በመቶ ለመቀነስ ተስማምተዋል
አሜሪካ፣ ካናዳ እና ኬንያ በዱባይ የስምምነቱ አካል ለመሆን ፊርማቸውን አኑረዋል
ከማቀዝቀዣ ቁሳቁሶች የምርት ሂደት እና ጥቅም ላይ በሚውሉበት ወቅት የሚፈጠር የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችለውን “የማቀዝቀዣ የቃልኪዳን ሰነድ” የፈረሙ ሀገራት ከ60 በላይ ሆኗል።
አሜሪካ፣ ካናዳ እና ኬንያም በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው 28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በዚሁ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ይህም ኮፕ28ን ለማቀዝቀዣ ቁሳቁሶች የአየር ብክለት ልዩ ትኩረት የሰጠ ጉባኤ አድርጎታል።
የምግብ ማቀዝቀዣ(ፍሪጅን ጨምሮ በቤት ውስጥ አየርን ለማቀዝቀዝ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪዎችን በማምረት፣ ጥቅም ላይ በማዋል እና በማስወገድ ሂደት የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ለመቀነስ ሀገራት ቃል ገብተዋል።
ከማቀዝቀዣ ቁሳቁሶች የሚለቀቀው ጋዝ በ2050 በአጠቃላይ ከባቢ አየርን ከሚበክሉ ጋዞች የ10 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ይገመታል።
ሀገራት ቃል በገቡበት ሰነድ ላይም የማቀዝቀዣ ቁሳቁሶችን የበካይ ጋዝ ልቀት በ2050 ከባለፈው አመት ከተመዘገበው በ68 በመቶ ለመቀነስ መስማማታቸው ተቀምጧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአየር ንብረት መልዕክተኛ ጆን ኬሪ “በሁሉም ዘርፎች የማቀዝቀዣ ቁሳቁሶች ብክለትን መቀነስ ይኖርብናል፤ ዘላቂ የሆኑና ከብክለት የጸዱ አማራጮን ማየትም ያስፈልጋል” ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ችግር ምድራችን በዚህ አመት ከፍተኛውን ሙቀት አስመዝግባለች።
በዚህም ምክንያት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ ሰዎች ሙቀትና ወበቅን የሚቀንሱ ማቀዝቀዣዎችን ይሻሉ፤ ይህ ፍላጎት በ2050 በሶስት እጥፍ እንደሚጨምርም ጥናቶች ያሳያሉ።
ፍላጎት እና አቅርቦቱ እስካሁን መጣጣም አለመቻሉን የሚያነሱ ባለሙያዎች፥ አቅርቦቱ ቢያድግም ይዞት የሚመጣው ፈተና አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
የክፕ28 ጉባኤም ከማቀዝቀዣ ቁሳቁሶች የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ለመቀነስ ተጨማሪ ሀገራት ቃል የገቡበት ሲሆን፥ ከብክለት በጸዱ የምግብና አየር ማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂዎች በስፋት እንዲተዋወቁም ተመክሮበታል።