በኮፕ28 ጉባኤ የመጀመሪያ አምስት ቀናት የ83 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል ተገብቷል
በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ እስካሁን 11 የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ የማድረግ ስምምነቶች ተደርሰዋል
ሀገራት የገቡትን ቃል ይፈጽሙ ዘንድም የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ጥሪ አቅርበዋል
በአረብ ኤምሬትሷ ዱባይ እየተካሄደ የሚገኘው 28ኛው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን ይዟል።
ጉባኤው በመጀመሪያ አምስት ቀናት ቆይታው ብቻ የ83 ቢሊየን ዶላር ቃል የተገባበት በመሆንም ታሪካዊ ሆኗል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ስራዎች ኤምሬትስ ያቋቋመችውን የ30 ቢሊየን ዶላር ፈንድ ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የድጋፍ ቃል መግባታቸውን የጉባኤው አዘጋጆች ተናግረዋል።
በጉባኤው እስካሁን የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትለው ችግር ምላሽ ለመስጠትና ለታዳሽ ሃይል ልማት 11 የቃልኪዳን ሰነዶች ተፈርመዋል።
በቀሪዎቹ ስድስት ቀናትም በርካታ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ለ”ግሪን ክላይሜት ፋይናንስ ፈንድ” የ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል የተገባበት ኮፕ28፥ በጣም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ ለተቋቋመው ፈንድም የ129 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አግኝቷል።
በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ ላተኮሩ ስራዎች ደግሞ ሀገራት የ7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ ስርአት እና በጤና ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ምላሽ ለመስጠት ፈንድ የተቋቋመበት የዱባዩ ጉባኤ፥ ለቴክኖሎጂ ሽግግርም የ568 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተገኝቶበታል።
ጉባኤው በቀጣይ ስድስት ቀናትም የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያደርሰው ጉዳትና ኪሳራ ምላሽ ለመስጠት ሀገራት እና ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የሚገቡበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ኮፕ28 እንደከዚህ ቀደሞቹ ጉባኤዎች ሀገራት የገቡትን የድጋፍ ቃል ከዱባይ ሲወጡ የሚዘነጉት እንዳይሆን በፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሱልጣን አልጀበር በኩል ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው።