የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ከብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ጋር መከሩ
ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ብራዚል ካስተናገደችው “የአማዞን ጉባኤ” ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል
በምክክራቸውም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት እና የአረብ ኤምሬትስ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር በብራዚል በተካሄደው “የአማዞን ጉባኤ” ተሳትፈዋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ሚኒስትሮች ጋር መክረዋል።
ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ከብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ጋር ሲመክሩ ብራዚል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የደን ጭፍጨፋን በ34 በመቶ መቀነሷን አድንቀዋል።
ሀገሪቱ ከኢንዶኔዥያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የሶስትዮሽ ትብብር በመፍጠር የአካባቢ ጥበቃ ላይ የጀመረችው ስራም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል።
ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ከኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፐትሮ ጋርም ከጉባኤው ጎን ለጎን ውይይት አድርገዋል።
ኤምሬትስ በቀጣዩ ህዳር ወር በምታዘጋቸው አለማቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) በአማዞን ጉባኤ ትኩረት የተሰጠው ነባር ህዝቦችን የደን ጥበቃ ንቅናቄ አካል የማድረግ መልካም ጅምር ንግግር ይደረግበታልም ነው ያሉት።
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃበር ከቦሊቪያው ፕሬዝዳንት ልዊስ ካታኩራ ጋርም የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ሊደረግ ስለሚገባው የፋይናንስ ድጋፍ ተወያይተዋል።
ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር የኮፕ30 አስተናጋጅ ከሆነችው ብራዚል የጤና ሚኒስትር ኔሲያ ትሪንዳድ ጋርም የጤና አጀንዳ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተሳስሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ውይይት አድርገዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ሃላፊ ራዛን አል ሙባረክ እና ሌሎች የአለማቀፍ ተቋማት መሪዎች እና የሀገራት ሚኒስትሮችም ከኮፕ28 ፕሬዝዳንት ጋር ለሁለት ቀናት ከተካሄደው የአማዞን ጉባኤ ጎን ለጎን መክረዋል።
አረብ ኤምሬትስ የአለማቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ28) ከፈረንጆቹ ህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 2023 ድረስ በዱባይ ታስተናግዳለች።