ኮፕ 28 የአየር ንብረት ፋይናንስ አለመግባባቶችን ለማስቆም ተስፋ ሰንቋል
የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ እስካሁን አልፈጸሙም
የበለጸጉ ሀገራት ደሀ ሀገራትን ከአየር ንብረት ቀውስ ለመከላከል የሚሰሩትን ስራ እየጎተቱ ነው ተባለ
የአየር ንብረት ፋይናንስ በዓለም የድርድር አጀንዳዎች ውስጥ ለበርካታ አስርት ዓመታት ግንባር ቀደም ነው።
ይህም የዓለም ሙቀት መጨመርን ለማሸነፍ የተያዙ ግቦችን ከማሳካት እና ወደ ንጹህ ኃይል ለመሸጋገር ወይም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በተጎጂ ሀገራት ለማላመድ ባለው ጠቀሜታ ምክንያት ነው።
መቀመጫውን ብሪታኒያ ያደረገው ኦክስፋም በአየር ንብረት ፋይናንስ ላይ ባደረገው አዲስ ጥናት የበለጸጉ ሀገራት ከእርዳታ ይልቅ ብድር በመስጠት ድሀና አቅመ ደካማ ሀገራት ከአየር ንብረት ቀውስ ለመከላከል የሚሰሩትን ስራ እየጎተቱ መሆናቸውን አመልክቷል።
ጥናቱ በተዘዋዋሪ መንገድ የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ለታዳጊ ሀገራት ለመክፈል ቃል የገቡት 100 ቢሊዮን ዶላር የተገደበ መሆኑንም ጠቁሟል።
- የአየር ንብረት ፋይናንስ ጉዳይን መፍታት በኮፕ28 ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው- ዶ/ር ሱልጣን አልጃበር
- የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃን ማፋጠን ለኢንቨስትመንትና ዘላቂ እድገት እድል ይፈጥራል- የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት
የአየር ንብረት ፋይናንስ በባለሞያዎችና ተሟጋቾች ሰፊ ክርክር አስነስቷል።
እ.አ.አ. በ1990ዎቹ የአየር ንብረት ድርድር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከቃሉ ፍቺ ጀምሮ አነጋጋሪነቱን ቀጥሏል።
የአየር ንብረት ፋይናንስን በተመለከተ ምንም አይነት ወጥነት ያለው ወይም ስምም ፍቺ የለም።
ይህ ፋይናንስ እንዴት መቅረብ እንዳለበትና ታዳጊ ሀገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ እና ለማላመድ ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል የሚለውም የተለያዩ እሳቤዎች ይንጸባረቅበታል። ጉዳዩ ለብዙ አስርተ ዓመታት ውዝግብ አስነስቷል።
በ2009 የበለጸጉ ሀገራት ከ2020 ጀምሮ ለአየር ንብረት ፋይናንስ በየዓመቱ 100 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር።
በዋናነት ታዳጊ ሀገራትን ከአየር ንብረት ተጽዕኖ እንዲያገግሙና የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ፈንዶችን ለማካተት ነው።
ነገር ግን የበለጸጉ ሀገራት በ2020፤ 83 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ስላቀረቡ ቃላቸው እስካሁን አልተፈጸመም።