ኮፕ28 ምን አሳካ? በቀጣይስ ምን ይጠበቃል?
ዱባይ ለ13 ቀናት ያስተናገደችው 28ኛው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታሪካዊ ስምምነት ተደርሶበታል
ጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ ለሚደርስ ጉዳትና ኪሳራ ስለሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍም ተመክሮበት ከ85 ቢሊየን ዶላር በላይ ቃል ተገብቶበታል
አረብ ኤምሬትስ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉበትን የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በስኬት አስተናግዳለች።
የጉባኤው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አልጀበር ታሪካዊው “የኤምሬትስ ስምምነት” ሲፈረም “በማውራት ሳይሆን በተግባር ማንነታችን አሳይተናል” ሲሉ ለደቂቃዎች ያለማቋረጥ የቀረበላቸው የጭብጨባ ውዳሴ ኤምሬትስ የሁለት ሳምንቱን ጉባኤ በብቃት እንደተወጣችው ማሳያ ነው።
የጉባኤው ስኬት በተፈረመው “የኤምሬትስ ስምምነት” ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ በየቀኑ ለውይይት የቀረቡት የውይይት አጀንዳዎች እና የተደረሱ ስምምነቶች የዱባዩን ጉባኤ በርግጥም ታሪካዊ ነው የሚያስብሉ ናቸው ይላል በዘናሽላል ጋዜጣ ትንታኔውን ያሰፈረው አየርላንዳዊ ጸሃፊ ጆኒ ዴኒ።
በጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ ስለድንጋይ ከሰል እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትና ኪሳራ መመከሩና ሀገራት ቃል የገቡት የ85 ቢሊየን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ብሎም ኤምሬትስ የ30 ቢሊየን ዶላር “አልቴራ” የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ይፋ ማድረጓንም ያወሳል።
ጉባኤው የነዳጅ አምራች ሀገርና የነዳጅ ኩባንያን የሚመሩ የኮፕ ፕሬዝዳንት ስኬታማ ጉባኤን ሊያስተናግዱና ሊመሩ አይችሉም በሚል ሲቀርቡ የነበሩ መሰረተቢስ መላምቶችንም ውድቅ ያደረገ መሆኑን አብራርቷል።
በኮፕ28 የተደረሰው የመጨረሻ ስምምነት አለማችን የበካይ ጋዝን በመቀነስ ደረጃ ከተቀመጠው ገደብ እንዴት እንደራቀች አመላክቶ የመፍትሄ ሃሳቦችንም አካቷል የሚለው ጆን ዴኒ፥ ረቂቁ ላይ ለቀናት ማሻሻያ ተደርጎ የኤምሬትስ ስምምነት መፈረሙንም ያወሳል።
ከፍተኛ ብክለትን የሚያስከትለውን የድንጋይ ከሰል እስከ 2050 ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በታዳሽ ሃይል ለመተካት ስምምነት መደረሱን በበጎ የሚያነሳው ጸሃፊው ስምምነቱ ሀገራትን አስገዳጅ አለመሆኑ ግን ስጋት ፈጥሮበታል።
የዱባዩ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ምድራችን ከተጋረጠባት ፈተና የሚታደጉ በርካታ ስምምነቶች የተደረሱበት ነው።
ይሁን እንጂ የጉባኤው ፕሬዝዳንት እንዳሳሰቡት ሀገራትና ኩባንያዎች የገቡትን ቃል መፈጸም ካልቻሉ የቢሊየኖችን ህይወት አደጋ ላይ የጣለው ጉዳይ አዳራሽ ከማሞቅ አያልፍም። እናም ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትና ኪሳራ እንዲሁም ለታዳሽ ሃይል ልማት ፋይናንስ የተገቡ ቃልኪዳኖች ሊፈጸሙ የግድ ነው ይላል በዘናሽናል ላይ ትንታኔውን የጻፈው አየርላንዳዊ ጆን ዴኒ።