ኮፕ28 ታሪካዊውን “የኤምሬትስ ስምምነት” አጸደቀ
የ197 ሀገራት ተወካዮች እና የአውሮፓ ህብረት ስምምነቱን ማጽደቃቸውን የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አልጀበር ተናግረዋል
28ኛ የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ በዛሬው እለት ይጠናቀቃል
ኮፕ28 በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ድርድር ሲደረግበት የቆየውን “የኤምሬትስ ስምምነት” አጸደቀ።
የ197 ሀገራት ተወካዮች በዚህ ታሪካዊ ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውም ተገልጿል።
የጉባኤው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር በድንጋይ ከሰል ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስምምነት የተደረሰበት ጉባኤ ከቀደምቶቹ ጉባኤዎች በበርካታ ጉዳዮች ልዩ እንደነበር አንስተዋል።
ከ83 ቢሊየን ዶላር በላይ የፋይናንስ ድጋፍ የተደረገበት ኮፕ28 የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታት ሀገራት በአንድነት ሲመክሩበትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ሲጠቁሙበት የቆየ እንደነበር አንስተዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትና ኪሳራ ለሚደርስባቸው አካላት ስለሚደረግ ድጋፍ በስፋት ተመክሮ ከስምምነት የተደረሰበት ጉባኤው በታዳሽ ሃይል ልማት ዙሪያም አመርቂ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ነው ያብራርሩት።
“ብዙዎች ይሄ ጉባኤ ስኬታማ አይሆንም ብለው ነበር፤ እኔ ግን ቃል ገብቸላችሁ ነበር፤ አካታች በሆነው ጉባኤ ሁሉም ተሳትፎ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ አሳክተነዋል፤ የኤምሬትስ ስምምነት ተፈርሟል” ሲሉም ተደምጠዋል።
በግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ በጤና እና ሌሎች ጉዳዮች የተፈረሙ ዲክላሬሽኖችም የኮፕ28 ጉባኤ ታሪካዊ እና ስኬታማነትን ያሳያሉ ነው ያሉት።
የታዳሽ ሃይል ልማትን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ከተደረሰው ስምምነት ባሻገር ለመጀመሪያ ጊዜ የድንጋይ ከሰል ጉዳይን በስምምነታችን ማካተታችንም ትልቁ ስኬት ነው ብለዋል።
የ”ኤምሬትስ ስምምነት” ምን ምን ጉዳዮችን አካቷል?
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ቢሮ 197 ሀገራት ተደራዳሪዎች እና የአውሮፓ ህብረት የተስማሙበትን የስምምነት ሰነድ በድረገጹ ላይ አውጥቷል።
በስምምነቱ ላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
1. በ2030 የታዳሽ ሃይል ልማትን በ2022 ከነበረበት በሶስት እጥፍ ማሳደግ፤ የሃይል አጠቃቀም ውጤታማነትን በ2030 በእጥፍ ማሳደግ፣
2. ቴክኖሎጂዎችን የማይጠቀሙና ጎጂ ጋዝ የሚለቁ የድንጋይ ከሰል የሃይል ምንጮችን በሂደት ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶችን ማፋጠን፣
3. እስከ2050 ድረስ ከካርበን ብክለት የጸዱ የሃይል ምንጮችን ለማስፋፋት የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር፣
4. በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ የድንጋይ ከሰልን ከያዝነው አመት ጀምሮ በፍትሃዊና አዋጭ በሆነ ሂደት ከኢነርጂ ስርአቱ ማስወጣት መጀመር፤
5. ብክለትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ የማዋሉን ሂደት ማፋጠን፣ የታዳሽ ሃይል ቴክኖሎጂዎች፣ የኒዩክሌር ኢነርጂ፣ የካርበን ማመቂያ እና ማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል፣
6. በ2030 ከካርበን ዳይ ኦክሳይድ ባሻገር እንደ ሚቴን ያሉ በካይ ጋዞችን ልቀት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ፣