የኮፕ28 ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ዛሬ ይቀርባል
ሀገራት “ታክቲካዊ መሰናክሎችን” በማስወገድና ልዩነታቸውን በማጥበብ ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተጠይቋል
የኮፕ28 የመጨረሻው የስምምነት ሰነድ በነገው እለት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል
28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ 12ኛ ቀኑን ሲይዝ የመጨረሻው ድርድር መካሄድ ይጀምራል።
የኮፕ28 ረቂቅ የስምምነት ሰነድ በዛሬው እለት ቀርቦ ተደራዳሪዎች ሲመክሩበት ይውላሉ ተብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ዋና ጸሃፊው ሲሞን ስቲልም በዚህ የድርድር ሂደት ወቅት ከስምምነት የሚያግዱ ጉዳዮች ሊወገዱ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የሀገራት ተደራዳሪዎች “ታክቲካዊ መሰናክሎችን” አስወግደውና የተወሰኑ ልዩነቶችን አጥብበው ስምምነቱን እንዲፈርሙም መጠየቃቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
“የኮፕ28 ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ዛሬ ይለቀቃል፤ አለምም ይመለከተዋል፤ የምንደብቅበት ስፍራ አይኖርም” ያሉት ሲሞን ስቲል፥
ተደራዳሪዎች ከተለመደው አዝጋሚ አካሄድ በመውጣት ሚሊየኖችን ሊያሳጣ ከሚችል አደጋ የሚጠብቅ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሳስበዋል።
የህገራት ተደራዳሪዎች ከዛሬ ጀምሮ የሚመክሩበት የኮፕ28 ረቂቅ የስምምነት ሰነድ በነገው እለት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰነዱ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ለመቀነስ ፍትሃዊና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ ሃሳቦችን ያካተተ እንደሚሆን ተገልጿል።
በነገው እለት ድርድሩ ተጠናቆ በይፋ ሲፈረም ዝርዝር ጉዳዮቹ ይታወቃሉ።