የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ የምርጫ ጉዳይ አይደለም - የኮፕ28 ፕሬዝዳንት
በአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች የከረረ አቋም የያዙ አካላትም የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል
በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አዲስ የስምምነት ሰነድ በነገው እለት ይፋ ይደረጋል
የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪዎች የያዙትን አቋም አለሳልሰው ከስምምነት እንዲደርሱ የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ጥሪ አቀረቡ።
በዱባይ ኤክስፖ ሲቲ እየተካሄደ በሚገኘው 28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በርካታ ስምምነቶች መደረሳቸውን ያወሱት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር፥ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ከስምምነት እንደሚደረስ ተስፋ አለኝ ብለዋል።
በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያደርሰው ጉዳትና ኪሳራ ብክለት የሚያስከትሉት ሀገራት በሚያዋጡት ገንዘብ ዙሪያ ከስምምነት ተደርሷል።
የነዳጅ እና ጋዝ ዘርፉ የሚለቀውን በካይ ጋዝ ለመቀነስም ስምምነት ተፈርሟል። በዚህ ስምምነት የአለማችን 40 በመቶ ብክለት የሚያስከትሉ 52 ኩባንያዎች መካተታቸውም የጉባኤው ሌላኛው ስኬት ነበር ብለዋል የኮፕ28 ፕሬዝዳንት።
በጉባኤው ተስፋ ሰጪ ስምምነቶች ሲደረሱ በርካታ አድካሚ ንግግሮች መደረጋቸውን በማውሳትም ለተደራዳሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአየር ብክለትን መቀነስ ምንም ምርጫ የማይቀመጥለት ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ሱልጣል አል ጀበር፥ በድርድር ላይ የሚገኙ ጉዳዮች በስምምነት እንዲጠናቀቁ ተደራዳሪዎች የከረረ አቋማቸውን እንዲያለዝቡ ጠይቀዋል።
በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ለተጎዱ ሀገራት ዘላቂ ማቋቋሚያ በሚውለው ፈንድ ዙሪያ ሀገራት የመጨረሻ ስምምነት ሊፈራረሙ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የኦፕ28 ጉባኤ ነገ 12ኛ ቀኑን ሲይዝ ለውይይት የሚቀርበው ሰነድ እንዲጸድቅም ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ዱባይ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።