የኮፕ 28 ረቂቅ ስምምነት ምን ምን አካቷል?
21 ገጾች ያሉት ረቂቅ የስምምነት ሰነድ የድንጋይ ከሰል ከጥቅም ውጭ የሚሆንበትን ሂደት አስቀምጧል
ለ13 ቀናት በአረብ ኤምሬትስ ዱባይ ሲካሄድ የቆየው ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል
የኮፕ28 ጉባኤ የመጨረሻውን ረቂቅ የስምምነት ሰነድ በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
የሀገራት ተደራዳሪዎች ሲመክሩበት የቆዩትና ዛሬ ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቀው ሰነድ 21 ገጾች አሉት።
ረቂቅ ሰነዱ የድንጋይ ከሰል ከጥቅም ውጭ የሚሆንበትን ሂደት ያመላከተ መሆኑን የኤምሬትሱ የዜና ወኪል ዋም ዘግቧል።
ከዚህም ባሻገር “የግሪንሃውስ ግዞችን ልቀት ለመቀነስና የአለም ሙቀት ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳይጨምር ጥልቅ፣ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሄዎች” እንዲተገበሩ ያሳስባል።
በሰነዱ የተካተቱ ስድስት ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
1. በ2030 የታዳሽ ሃይል ልማትን በ2022 ከነበረበት በሶስት እጥፍ ማሳደግ፤ የሃይል አጠቃቀም ውጤታማነትን በ2030 በእጥፍ ማሳደግ፣
2. ቴክኖሎጂዎችን የማይጠቀሙና ጎጂ ጋዝ የሚለቁ የድንጋይ ከሰል የሃይል ምንጮችን በሂደት ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶችን ማፋጠን፣
3. እስከ2050 ድረስ ከካርበን ብክለት የጸዱ የሃይል ምንጮችን ለማስፋፋት የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር፣
4. በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ የድንጋይ ከሰልን ከያዝነው አመት ጀምሮ በፍትሃዊና አዋጭ በሆነ ሂደት ከኢነርጂ ስርአቱ ማስወጣት መጀመር፤
5. ብክለትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ የማዋሉን ሂደት ማፋጠን፣ የታዳሽ ሃይል ቴክኖሎጂዎች፣ የኒዩክሌር ኢነርጂ፣ የካርበን ማመቂያ እና ማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል፣
6. በ2030 ከካርበን ዳይ ኦክሳይድ ባሻገር እንደ ሚቴን ያሉ በካይ ጋዞችን ልቀት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ
ለ13 ቀናት በዱባይ ሲካሄድ የቆየው 28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ በዛሬው እለት ይጠናቀቃል።