በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለታዳጊ ሀገራት ይዋጣ የተባለው 100 ቢሊዮን ዶላር በመሟላት ላይ መሆኑ ተገለጸ
የፋይናንስ እና የልማት ተቋማት ግን ገንዘብ ማዋጣት አልጀመሩም ተብሏል
በቻይና የሚመራው 77 አባላት ያሉት የታዳጊ ሀገራት ስብስብ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮፕ28 ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለታዳጊ ሀገራት ይዋጣ የተባለው 100 ቢሊዮን ዶላር በመሟላት ላይ መሆኑ ተገለጸ።
ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ ከፍተኛ ሙቀት በማስተናገድ ላይ ስትሆን ባሳለፍነው ሳምንት በታሪክ ሞቃታማውን እለት አሳልፈናል።
የዓለም ሙቀት በጨመረ ቁጥርም የተፈትሮ ሚዛንን ከሚያስጠብቁት አንዱ የሆነው ግግር በረዶ እየቀለጠ ወንዞች እና መሬት በጎርፍ በመጥለቅለቅ ላይ ናቸው።
እንደ አፍሪካ እና እስያ ያሉ ሀገራት ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቀው በካይ ጋዝ መጠን ላይ ዝቅተኛ አበርክቶ ቢኖራቸውም የከፋ ድርቅ እና ጎርፍ እያስተናገዱ ናቸው ተብሏል።
ይህን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ለማካካስ ከ15 ዓመት በፊት በፈረንሳይ ፓሪስ በተደረገ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ቢወሰንም ይህ ውሳኔ እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም።
የፊታችን ሕዳር በተባበሩት አረብ ኢምሬት ኮፕ28 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ይካሄዳል።
በዚህ ጉባኤ ላይ ከ15 ዓመት በፊት የተወሰነው ከበለጸጉ ሀገራት ኢንዱስትሪዎች በሚለቀቅ በካይ ጋዝ ምክንያት ታዳጊ ሀገራት ላይ ለደረሰባቸው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፈል የተላለፈው ውሳኔ አፈጻጸም ይዘጋጅለታል ተብሏል።
የጉባኤው ፕሬዝዳንት እና የአረብ ኢምሬት ኢንዱስትሪ ሚንስትር ዶክተር ሱልጣን አልጃቢር እንዳሉት ለታዳጊ ሀገራት ክከፈል የተባለው የ100 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ገንዘብ እየተዋጣ መሆኑን ተናግረዋል ።
ይሁንና የፋይናንስ እና የልማት ድርጅቶች የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ካሳ ገንዘብ ቢያዋጡ የካሳ ክፍያ መጠኑ በትሪሊዮን ዶላር ሊሆን እንደሚችልም ዶክተር ሱልጣል አክለዋል።
በዚህ ጉባኤ ላይ በቻይና የሚመራው እና ከዓለም ህዝብ የ80 በመቶ ድርሻ ያለው ቡድን 77 ሀገራት በኮፕ28 ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።