የኮፕ28 ተሳታፊዎች ስለጉባኤው ምን አሉ?
ጉባኤው ይበልጥ መተማመን የሚፈጥርና ከ2015 በኋላ ትልቅ ስምምነት የሚደረስበት እንደሚሆን ተሳታፊዎቹ ለአል ዐይን ተናግረዋል
በድንጋይ ከሰልና ነዳጅ የአየር ንብረት ለውጥ ድርሻ ዙሪያም ግልጽ ምክክር እንዲደረግ ጠይቀዋል
28ኛው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በትናንትናው እለት በይፋ ተጀምሯል።
ጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ማንም የማይገፋበትና አካታች የሚሆንበት፤ የድንጋይ ከሰል የአየር ንብረት ለውጥ ድርሻም በግልጽ የሚመከርበት ነው።
ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጉባኤው ተሳታፊዎችም ይህ አካታች እና ግልጽ የውይይት መድረክ ከቀደሙት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች የተለይ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር የኮፕ28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውና እስካሁን ያከናወኗቸውን ተግባራትም አድንቀዋል።
በጉባኤው ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የአለም የሙቀት መጠን ጭማሬ ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳይበልጥ የመገደብ ጉዳይ የሀገራት መሪዎች ትኩረት ሰጥተውት የመፍትሄ እርምጃዎችን ሊያስቀምጡ እንደሚገባም ነው ያነሱት።
የአለም ሙቀት ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ከጨመረ 50 በመቶ የአለም ግግር በረዶ ቀልጦ በ2100 የባህር ጠለል ወለል ከፍታ በ9 ሴንቲሜትር ከፍ እንደሚል ጥናቶች ያመላክታሉ።
በኮፕ28 ጉባኤ እየተሳተፈ የሚገኘው አሌክሳንደር አኮቢ “ምድራችን የማትወጣው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ በፊት የሙቀት መጨመርን ለመገደብም ሆነ በካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የጋራ ርብርብ ያስፈጋል” ብሏል።
ከባቢ አየርን በመበከል ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለውን የድንጋይ አክሰል ጥቅም ላይ እንዳይወል በዱባይ የሚጀመረው ድርድርም በቀጣይ ውጤት እንደሚያመጣ ገልጿል።
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበርም በኮፕ28 ጉባኤ ለውይይት የማይቀርብ አጀንዳ የለም ያሉ ሲሆን፥ የድንጋይ ከሰል የአየር ብክለት ጉዳይም ይመከርበታል ብለዋል በመክፈቻ ንግግራቸው።
አሜሪካዊው የጉባኤው ተሳታፊ ራሻ ሃሳኒን እንደሚለው የድንጋይ ከሰልን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ የሚደረገው ንግግር ግልጽ የሽግግር ጊዜ ማስቀመጥና አማራጭ የታዳሽ ሃይል ልማትን መደገፍ ያስፈልጋል ባይ ነው።
በኮፕ28 ጉባኤ የኢነርጂ ኩባንያዎች መሳተፍ መጀመራቸው መተማመን ለመፍጠርና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለመቀየስ እንደሚስችልም በመጥቀስ።
ትናንት በዱባይ ኤክስፖ ሲቲ በይፋ የተጀመረው 28ኛው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ ሲውል የሀገራት መሪዎች የሚያደርጉት ንግግር ይጠበቃል።