አሜሪካ 'ለግሪን ክላሜት ፈንድ' 3 ቢሊዮን ዶላር ልታዋጣ መሆኑ ተገለጸ
በፈረንጆቹ 2010 የተቋቋመው ይህ ፈንድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የሚለው ግዙፍ አለምአቀፍ ፈንድ ነው
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ዘሪስ በዛሬው እለት በዱባይ እየተካሄደ ባለው የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ቃል የተገባውን ገንዘብ ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል
አሜሪካ 'ለግሪን ክላይሜት ፈንድ' 3 ቢሊዮን ዶላር ልታዋጣ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በፈረንጆቹ 2010 የተቋቋመው ይህ ፈንድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የሚውለው ግዙፍ አለምአቀፍ ፈንድ ነው። ለዚህ ፈንድ እስካሁን ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቃል ተገብቷል።
አሜሪካ ልትሰጥ ያሰበችው 3 ቢሊዮን ዶላር ከዚህ በፊት ለፈንዱ ከሰጠችው 2 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ዘሪስ በዛሬው እለት በዱባይ እየተካሄደ ባለው የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ቃል የተገባውን ገንዘብ ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን በመወከል በኮፕ28 ስብሰባ እየተካፈሉ ያሉት ሀሪስ የአየር ንብረት መልክተኛውን ጆን ኬሪን እና በደርዘን የሚቆጠሩ ኃላፊዎችን የያዘው የልኡካን ቡድን አካል ናቸው።
በአረብ ኢምሬትስ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የኮፕ28 ስብሰባ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
የኮፕ28 ስብሰባ ከአለም ትልቁ የአየር ንብረት ጉባኤ ሲሆን ከ198 ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮች(መሪዎች ወይም ባለስልጣናት) እና ግብረሰናይ ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።