ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጮችን መደገፍ እንደሚገባ የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
ህብረተ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ማካካሻ ፈንድ ገንዘብ እንደሚያዋጣም አስታውቋል
የኮፕ28 ዓለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥ በአረብ ኢምሬት ዱባይ እየተካሄደ ይገኛል
ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጮችን መደገፍ እንደሚገባ የአውሮፓ ህብረት ገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር ይመክራል፡፡
ይህ ጉባኤ በተመድ አባል ሀገራት እየተዟዟረ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት በዱባይ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደርሊን እንዳሉት በአየር ንብረት ለውጥ የበለጠ ተጋላጭ የሁኑ ሀገራትን መደገፍ ይገባል ብለዋል።
በዱባይ እየተካኬደ ያለው ኮፕ28 ጉባኤ ለምድራችን ጠቃሚ ጉባኤ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶችን መቀነስ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
አውሮፓን ጨምሮ ሁሉም የዓለም ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ ሚቴን ጋዝን መቀነስ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ማካካሻ ፈንድ ሊዋጣ ለታሰበው 100 ቢሊዮን ዶላር አውሮፓ ህብረትም የሚጠበቅበትን የገንዘብ መጠን እንደሚያዋጣም ቮንደርሊን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም የአረንጓዴ ቦንድ እና ካርቦን ክፍያ ስርዓት ሊጀምሩ እንደሚገብም ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።
ለቀጣዮቹ 10 ቀናት የሚቆየው ኮፕ28 ጉባኤ ላይ 500 ሺህ ሰዎች እየተሳተፉበት ይገኛል።
በዚህ ጉባኤ ላይ የ200 ሀገራት መሪዎች፣ ሚንስትሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ተጋባዥ ሰዎች እየተሳተፉ ናቸው።
በአረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የዘንድሮው ኮፕ28 የተመድ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በ2015 በተካሄደው ከፓሪስ ስምምነት በኋላ ውጤታማ መድረክ እንደሆነ ተገልጿል።