በካይ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት ለመለገስ ቃል የገቡትን 100 ቢሊየን ዶላር ሊሰጡ ይገባል - አል ጃበር
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት በህዳር ወር መጨረሻ በዱባይ የሚካሄደው ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን የአለም ሀገራት በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል
ከ170 በላይ ከመላው አለም የተውጣጡ ሚኒስትሮችና ተደራዳሪዎች በአቡ ዳቢ እየመከሩ ነው
በዱባይ የሚካሄደው አለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ28) የተሳካ እንዲሆን ሀገራትን ማስተባበር እንደሚገባ የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ገለጹ።
የአየር ንብረትን እየበከሉ የሚገኙ ሀገራት ለታዳኒ ሀገራት ለመለገስ ቃል የገቡትን 100 ቢሊየን ዶላር መስጠት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ይህን ያሉት በህዳር ወር መጨረሻ ከሚካሄደው ጉባኤ አስቀድሞ በሚደረገው የሚኒስትሮች እና ተደራዳሪዎች ምክክር ላይ ነው።
በአቡ ዳቢ እየተካሄደ በሚገኘው ስብሰባ ላይ ከ100 በላይ የሀገራት ተደራዳሪዎች እና 70 ሚኒስትሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው ተብሏል።
ይህም ከቀደሙት የቅድመ ጉባኤ የሚኒስትሮች ስብሰባዎች ከእጥፍ በላይ ተሳታፊዎች የተመዘገቡበት ሆኗል።
ዶክተር ሱልጣን በዚህ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ስምምነት እንዲደረስ እየሰራ ነው ብለዋል።
ኤምሬትስ በአየር ንብረት ለውጥ እና ልማት ዙሪያ ሀገራትን በትብብር መንፈስ ለማቀራረብም እየተጋች እንደምትገኝ አብራርተዋል።
አለም በተለያዩ ምክንያቶች መከፋፈል ውስጥ ብትገባም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ግን በአስቸኳይ የጋራ አቋም ይዛ መንቀሳቀስ እንዳለባትም ነው ያሳሰቡት።
አለማቀፉ ማህበረሰብ ተስፋ፣ ወንድማማችነት፣ መረጋጋት እና ሰብአዊ ልዕልናን የሚደግፍ ግልጽ መልዕክትን በዱባዩ ጉባኤ እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃልም ብለዋል።
በጉባኤው እየጨመረ የመጣውን የአለም ሙቀት ለመቆጣጠር የተደረሰው ስምምነት እንዲከበር ቃል ከመግባት የተሻገረ ተግባርን ለመከወን መግባባት ላይ እንደሚደርስም አምናለሁ ነው ያሉት።
ዛሬ በአቡዳቢ የተጀመረው የኮፕ28 ጉባኤ የሚኒስትሮችና ተደራዳሪዎች የምክክር መድረክ እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን በጉባኤው ላይ የሚተኮርባቸው አጀንዳዎች ይለዩበታል ተብሎ ይጠበቃል።