ሁለት ቢሊዮን ያህሉ የዓለማችን ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት መሆኑን እንደማይቀበሉ ተገለጸ
ዓለም አሁንም የአየር ንብረት ለውጥ የጋራ ስጋት መሆኑ ላይ የጋራ አቋም እንዳልያዘ ተገልጿል
አውሮፓውያን ከሌሎች በተሻለ መልኩ የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ስጋታቸው እንደሆነ ያምናሉ ተብሏል
ሁለት ቢሊዮን ያህሉ የዓለማችን ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት መሆኑን እንደማይቀበሉ ተገለጸ።
የአየር ንብረት ለውጥ በየዕለቱ በዜጎች ላይ ስጋት በደቀነበት ባሁኑ ወቅት አሁንም ቢሊዮኖች እንደስጋትነት አይቀበሉትም ተብሏል።
ጋሉፕ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የዓለም አደጋ ተጋላጭነት ጥናት ተቋም ባስጠናው ጥናት መሰረት ሁለት ቢሊዮን የዓለማችን ህዝቦች የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ስጋታቸው እንዳልሆነ እንደሚያምኑ ተገልጿል።
በ121 ሀገራት የሚገኙ ከ126 ሺህ በላይ ዜጎች በተሳተፉበት በዚህ ጥናት መሰረት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ስጋታቸው እንዳልሆነ ያምናሉ ተብሏል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ አውሮፓዊያን የአየር ንብረት ለውጥ ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት ዋነኛ ስጋታቸው እንደሆነ ያምናሉ።
በተለይም ጣልያን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስፔን፣ ቺሊ፣ ግሪክ፣ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቹጋል፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጀርመን የአየር ንብረት ለውጥ የምድራችን ዋነኛ ስጋት ነው ብለው ከፍተኛ እምነት ያሳደሩ ሀገራት ናቸው።
በአጠቃላይ 75 በመቶ የዓለማችን ህዝብ ቀጣዮቹ 20 ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ይፈተናል ብለው እንደሚያምኑ ተገልጿል።
ዜጎችን ስለ አየር ንብረት ለውጥ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዙ ትምህርት ትልቅ መሳሪያ ነው የተባለ ሲሆን ሀገራት በትምህርት ስርዓታቸው ውስጥ ስለ አየር ንብረት ምንነት ሊያስተምሩ ይገባልም ተብሏል።