የአየር ንብረት ፋይናንስ ጉዳይን መፍታት በኮፕ28 ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው- ዶ/ር ሱልጣን አልጃበር
የአፍሪካ የአየር ንብረት ፋይናንስ ፍትሃዊነት ጉደይ የዓለም ትኩረት መሆን አለበት ብለዋል
በ20 ዓመታት በኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስት ከተደረገ 3 ትሪሊየን ዶላር ውስጥ ለፍሪካ የደረሰው 2 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል
የአየር ንብረት ፋይናንስ ጉዳይን መፍታት በኮፕ28 ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የኮፕ-28 ፕሬዝዳንትና የአረብ ኢሚሬትስ የኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሱልጣን አል ጃበር (ዶ/ር) አስታወቁ።
ዶ/ር ሱልጣን አልጃበር በግብጽ ሻርም አልሼክ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ልማት ባንክ የአመራሮች ቦርድ ዓመታዊ ስብስባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም የአረብ ኢሚሬትስ ፕሬዝዳነት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ መልእክት ያስተላለፉት ዶ/ር ሱልጣን አልጃበር ፕሬዝዳንቱ ለዘላቂ ልማት እና የአየር ንብረት እርምጃ ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ዶ/ር ሱልጣን አልጃበር አክለውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካ በዓየር ንብረት ዙሪያ ፍትሃዊ ፋይናንስ ማግኘት ላይ ትከረት በማድረግ ከስምምነት መደረስ አለባቸው ብለዋል
አፍሪካ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ሀብታም አህጉር ነች ያሉት ዶ/ር ሱልጣን፤ በተለይም አህጉሩ በንፋስ ኃይል፣ በጸሃይ ኃይል፣ በውሃ እና በጂኦተርማል የኃይል ምንጮች ዘርፍ ከፍተኛ ሀብት አለው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህም አፍሪካ ዝቅተኛ የካርቦን እድገትን እና ዘላቂ ልማትን ለማስመዝገብ ትልቅ አቅም እንዳላት የሚያረጋግጥ ቢሆንም የሚፈለገውን እድገት የሚያደናቅፍ መሰረታዊ ፈተና አለ ይህም የፋይናንስ እጥረት ነው ብለዋል።
የገንዘብ እጥረቱ በአፍሪካ የአለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃ እና ዘላቂ ልማት ግቦችን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ጠቁመው ይህንን ጉዳይ መፍታት ከኮፕ28 ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፤ ይህንን ከግብ ለማድረስ ከሁሉም አካላት ጋር እንሰራለን ብለዋል።
አል ጃብር አክለውም የአፍሪካ ሀገራት ከአጠቃላይ የዓለም አቀፍ የካርቦት ልቀት ውስጥ 4 በመቶውን ድርሻ ብቻ ይይዛሉ፤ ነገር ግን ከፍተኛ ተጎጂዎች 54ቱም የአፍሪካ ሀገራት ናቸው ያሉት ዶክተር ሶልጣን፤ በአየር ንብረት ሳቢያ የአፍሪካ አህጉር እስከ 15 በመቶ የጂዲፒ እድገቷን ታጣች ብለዋል።
በታዳሽ ኃል ዘርፍም ባለፉት 20 ዓመታት በዓለም ዙሪያ ኢንቨስት ከተደረገ 3 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ ለአፍሪካ የደረሰው 2 በመቶው ብቻ እንደሆነ እና ይህም ፍትሃዊ እንዳልሆነም ነው ዶ/ር ሱልጣን አልጃበር ያስታወቁት።
ዶ/ር ሱልጣን በንግግራቸው አክለውም በአየር ንብረት የገንዘበ ድጋፍ ለአፍሪካ የሚደርሰው ዓመታዊ የገንዘብ መጠን 30 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ የገንዘብ መጠን በ10 እጥፍ ማደግ እንዳለበትም አስታውቀዋል።
በአረብ ኢሚሬትስ በሚካሄደው ኮፕ28 የአየር ንብረት ጉባዔ ላይም የፋይናንስ ጉዳይን መፍታት በኮፕ28 ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።