የኮፕ- 28 ፕሬዝዳንት ሱልጣን አል ጃበር ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር ተወያዩ
ፓሪስ በ2015 የዓለም ሙቀት መጨመርን በ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ ከስምምነት የተደረሰባት ታሪካዊ ከተማ ናት
ዶ/ር አል ጃበር በዓለም አቀፉ የኢነርጂ “ እድገት የሚመጣው በአጋርነት እንጂ በፖላራይዜሽን አይደለም” ብለዋል
የኮፕ-28 ፕሬዝዳንትና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ መልዕክተኛ ዶ/ር ሱልጣን አል ጃበር ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያዩ ።
ውይይታቸው የፈረንሳይ እና የተባበሩት አረብ አሚሬትስ ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበርም ተገልጿል።
ፓሪስ በፈረንጆች 2015 የዓለም ሙቀት መጨመርን በ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ ከስምምነት የተደረሰባት ታሪካዊ ከተማ መሆኗ ይታወቃል።
ዶ/ር አል ጃበር በአሁኑ የፓሪስ ቆይታቸውም ከማክሮን ጋር የፓሪሱ ስምምነት ግቦች እንዴት ማሳካት እንደሚቻል መወያየታቸውንም ነው የኮፕ-28 ኦፊሴላዊ የትዊተር ገጽ መረጃ የሚያመላክተው።
ዶ/ር አል ጃበር በሰኔ ወር በፓሪስ ሊካሄድ በታቀደው አዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንሺያል ስምምነት ስብሰባ ላይ ከፈረንሳይ ጋር አብሮ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማክሮን አረጋግጠውላቸዋል ።
"ይህ ከኮፕ-28 በፊት ወሳኝ ምዕራፍ ይሆናል"ም ነው ያሉት ዶክተር አል ጃበር።
በሚኖረው መድረክ በኮፕ-28 ላይ እውነተኛ እርምጃ እንዴት እንደሚወስድ በግልጽ ማሳወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።
"ይህ የግል ፋይናንስን በማሰባሰብ፣ ኮንሴሲሺናል ፋይናንስን ማሳደግ እና የካርበን ገበያዎችን በማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግንይጨምራል"ያሉትዶ/ር አል ጃበር : ሴክተሮች አንድ ላይ ሆነው እድገትን ማምጣት እንዳለባቸውም አጽንዖት ሰጥተዋል።
"ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች - መንግስታት፣ የግሉ ሴክተር እና የሲቪል ማህበረሰቦች - በአንድነት በአንድ አቅጣጫ መምራት እንፈልጋለን" ሲሉም አክለዋል ።
ዶ/ር አል ጃበር በዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር “ለመከፋፈል ቦታ የለም። እድገት የሚመጣው በአጋርነት እንጂ በፖላራይዜሽን አይደለም። አንድ ላይ ከሰራን ከመጀመሪያው የኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ በሰው ልጅ እና በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ትልቁን ለውጥ ማምጣት እንደምንችል በእውነት አምናለሁ" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አረብ ኢሚሬትስ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ተቀብለው ከፈረሙ የቀጣናው ሃገራት መካከል ቀዳሚዋ መሆኗ ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም በ2050 የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ያላትን ራዕይ ይፋ ያደረገችና ወደ ተግባር የገባች የመጀመሪያዋ ሀገር ነች ፡፡