አረብ ኤምሬትስ እና ጣሊያን በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ እና የአረብ ኤምሬትስ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሱልጣን አል ጀበር ስምምነቱን ተፈራርመዋል
ጣሊያን በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ በስፋት እየሰራች ካለችው ኤምሬትስ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል
አረብ ኤምሬትስ እና ጣሊያን በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የአረብ ኤምሬትስ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር እና የጣሊያን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ ናቸው የተፈራረሙት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፥ ሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን የሚያሳድግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ሲያሳድጉም ለአየር ንብረት ለውጥ እኩል ትኩረት ሰጥተው ለመስራት መስማማታቸውን ነው የጠቆሙት።
- የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ 2023ን "የዘላቂነት ዓመት" በሚል አወጁ
- ቦይንግ ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ በታዳሽ ሀይል የሚሰሩ አውሮፕላኖችን እንደሚያመርት አስታወቀ
የኤምሬትስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው የአቡዳቢ ብሄራዊ የነዳጅ ኩባንያ እና የጣሊያኑ ኢ ኤን አይ የነዳጅ ኩባንያ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ የካርበን ልቀትን በመቀነስና የኢነርጂ ዘርፉ ላይ በሚደረጉ ሽግግሮች ዙሪያ ያተኮሩ ሃሳቦችን ማካተቱ ተጠቅሷል።
ሁለቱ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች የተፈራረሙት የትብብር ሰነድ፥ የሃይል አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ከማድረግ በዘለለ የካርበን ልቀታቸው የቀነሰ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ያግዛል ተብሏል።
ጣሊያን እና ኤምሬትስ በካርበን አማቂ ቴክኖሎጂዎች፣ በታዳሽ እና ንጹህ የሃይል አማራጮች ዙሪያም በትብብር መስራት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች መፈራረማቸውን ዋም አስነብቧል።
የጣሊያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) ፕሬዝዳንት ሆነው ለተመረጡት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።