ዩኤኢ "COP-28"ን ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ ድጋፍ አገኘ
28ኛው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ /COP-28/ በፈረንጆቹ ህዳር 2023 በአቡዳቢ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ይጠበቃል
ዩኤኢ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ተቀብለው ከፈረሙ የቀጣናው ሀገራት መካከልም ቀዳሚዋ ነች
የተባሩት አረብ ኢሚሬቶች /ዩ.ኤ.ኢ/ በፈረንጆቹ በ2023 "COP-28" የአየር ንብረት ጉባዔ ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ ድጋፍ ማግኘቱን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል-ናህያን ገለጹ።
በግላስጎው እየተካሄደ ባለው COP-26 የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ያለውን የዩኤኢ ልዑክ በመምራት በስኮትላንድ የሚገኙት ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል-ናህያን፤ ዩኤኢ COP-28ን እንድታዘጋጅ ድጋፋቸውን የሰጡ አጋ ሀገራትን አመስግነዋል።
በዛሬው እለትም የኤዥያ-ፓሲፊክ ቡድን አባል ሀገራት፤ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች 28ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (COP-28) ጉባኤን ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ እንደሚደግፉ አስታውቋል።
ሀገራቱ የዩኤኢን ጥያቄ እንደሚደግፉ ያስታወቁት፤ የፓሪሱን ስምምነት እና የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም ስራን ለማፋጠን የሚረዱ ዘዴዎችን ለመወያየት በስኮትላንዷ ግላስጎው ከተማ እየተካሄደ ባለው የCOP-26 ላይ ነው።
ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል-ናህያን: "የኤዥያ-ፓሲፊክ ቡድን አባል ሀገራት ጨምሮ ሁሉንም አጋሮቻችን ለሰጡን ድጋፍ ላቅ ያለ ምሰጋና አለን" ብለዋል።
በስኮትላንድ ግላስኮው እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው Cop-26 ፤ 30 ሺ ያህል ታዳሚዎች እየተሳተፉበት ያለ ነው።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) እ.ኤ.አ የ2023ን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔን (Cop-28) በአቡዳቢ ለማዘጋጀት ከአራት ወራት በፊት ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል።
በዚህም ዩኤኢ በግላስጎው እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ባገኘችው ድጋፍ መሰረት፤ 28ኛውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንደፈረንጆቹ ህዳር 2023 በአቡዳቢ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ሼክ አብዱላህ ጉባዔው በዘርፉ ያለውን እድል ለመጠቀም የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል ያሉ ሲሆን፤ ከሀገራት ጋር ተባብረው እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ከባድ ተጽዕኖን ሊያሳርፍ ቢችልም የስራ ዕድል ሊፈጠርበት እንደሚችል ይታመናል። ዩኤኢ ለኢነርጂ ዘርፍ አማራጮች ትኩረት መስጠቷንና በዘርፉ ብዙ ሀብት ፈሰስ ማድረጓን የዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው።
ዩኤኢ የዓለም አቃፍ ታዳሽ ኃይል ዓመታዊ ጉባዔ ቋሚ አዘጋጅ ነች። የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ተቀብለው ከፈረሙ የቀጣናው ሃገራት መካከልም ቀዳሚዋ ነች። ግዙፍ የፀሃይ ኃይል አማራጮችን ከገነቡና በርካሽ ከሚያቀርቡ ሀገራት መካከልም ናት።
ለታዳሽ ኃይል ግንባታዎች ትኩረት ሰጥታ የምትሰራው ዩኤኢ በ6 አህጉራት በሚገነቡ የታዳሽ ኃይል ልማት ፕሮጄክቶች ላይ 17 ቢሊየን ዶላር ገደማ ገንዘብን ፈሰስ አድርጋለች።
በተለያዩ አጋሮቿ በኩል በድጋፍና ብድር መልክ 1 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ ማድረጓንም መረጃዎች ያመለክታሉ።